ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በተደረጉ የፋይናንስ እና ካፒታል ገበያ ዘርፎች ላይ በኔዘርላንድስ ለሚገኙ አምራች ኩባንያዎች ማብራሪያ ተሰጠ

76

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በቅርቡ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በተደረጉ የፋይናንስ እና ካፒታል ገበያ ዘርፎች ላይ በኔዘርላንድስ ለሚገኙ አምራች ኩባንያዎች ማብራሪያ ተሰጠ፡፡

ማብራሪያውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ናቸው፡፡

በአቶ ዳጋቶ ኩምቤ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም “የአፍሪካ አረንጓዴ ኢንደስትሪያላይዜሽን - በአፍሪካ የተሰራ” በሚል መሪ ሀሳብ በብራሰልስ በተዘጋጀው ’AFRICA 20 Works! 24’ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሁነት ላይ ተካፍሏል፡፡

የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሁነቱ በኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በኔዘርላንድስ አፍሪካ የቢዝነስ ካውንስል አማካኝነት መዘጋጀቱን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡


 

በሁነቱም በመንግስት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራባቸው ባሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እና አማራጮች ዙሪያ እንዲሁም በሁነቱ መሪ ቃል ላይ ያተኮረ ገለጻ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በተደረጉ የፋይናንስ እና ካፒታል ገበያ ዘርፎች ላይ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠታቸውም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

በቤልጂየም የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ እና ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውም ተጠቁሟል፡፡

በሁነቱ ከተሳተፉ አምራች ኩባንያዎች እና ባለሀብቶች ጋር የአንድ ለአንድ ውይይት መደረጉም ተመላክቷል፡፡

ልዑኩ በኔዘርላንድስ በተለይም በአግሮ ሎጀስቲክስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራች ድርጅቶችን መጎብኘቱም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም