የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይካሄዳሉ 

192

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ።

የመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ መድን መካከል ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይከናወናል።

በሩብ ፍጻሜው ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 1 እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን አዳማ ከተማን 3 ለ 1 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ ጨዋታው ቀርበዋል።

ወላይታ ድቻ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ደሴ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕናን ማሸነፉ ይታወቃል።

ክለቡ በኢትዮጵያ ዋንጫ ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ግቦችን አስተናግዷል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በውድድሩ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ እና አርሲ ነገሌን አሸንፏል።

ኢትዮጵያ መድን እስከ አሁን በኢትዮጵያ ዋንጫ ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 3 ግቦችን አስተናግዷል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ28 ነጥብ 11ኛ፤ ኢትዮጵያ መድን በ22 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። 

በሌላኛው የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ መርሐ ግብር ነገ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም እንደሚደረግ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

የፍጻሜው ጨዋታ የሚደረግበት ቀንና ቦታ በቀጣይ ይፋ እንደሚሆንም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ በቀጣዩ ዓመት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት አራት ዓመታት ሳይካሄድ የቆየ ሲሆን በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሲሳተፍ ቆይቷል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም