በደቡብ ኦሞ ዞን ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

89

 ጂንካ፤ ሚያዚያ 18/2016 (ኢዜአ) ፡ - በደቡብ ኦሞ ዞን ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጋዲ በርቂ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ B3-65858 በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ተደብቀው ሲጓጓዙ በነበረበት ወቅት ነው።

ተሽከርካሪው በደቡብ ኦሞ ዞን ከዳሰነች ወረዳ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ እንደነበረም አመልክተዋል። 

በወረዳው በቱርሚ እና በዲመካ ከተማ መካከል በሚገኝ ጫካ ውስጥ የሰሌዳ ቁጥሩን ለመቀየር ተሽከርካሪው በቆመበት ወቅት የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ከነአሽከርካሪው መያዛቸውን ተናግረዋል።

በተሽከርካሪው ቀደም ሲል ተለጥፎ የነበረውን የአዲስ አበባ ሰሌዳ ቁጥር በደቡብ ክልል ሰሌዳ ቁጥር ለመቀየር ሙከራ መደረጉን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ጋዲ፣ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ትናንት ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ በፖሊስ ሊያዝ ችሏል ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በኮንትሮባንድ ሲጓጓዝ የተያዙት ንብረቶች 7ሺህ 288 የሞባይል ስልኮች እና 3ሺህ 140 የሞባይል ባትሪዎች ናቸው።

ለኮንትሮባንድ እቃዎቹ መያዝ የህብረተሰቡና የፖሊስ ቅንጅት ፋይዳ የጎላ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተሩ፣ የተሽከርካሪው ረዳት ለጊዜው መሰወሩን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ባደረገው አሽከርካሪ ላይ የምርመራ ሥራ መጀመሩንም ዋና ኢንስፔክተር ጋዲ ጨምረው ገልጸዋል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትል ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም