በክልሉ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በተደረገ ጥረት ውጤት ተመዝግቧል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

95

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት  ውጤት መገኘቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ክልል አቀፍ የኑሮ ውድነት ማረጋጋትና የክህሎት-መር ሥራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በተደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤት ተመዝግቦበታል።

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ክልሉ ያለውን ሰፊ ፀጋና አቅም በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ምርትና ምርታማነት በመጨመር፣የገበያ አማራጮችን በማስፋት እንዲሁም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር የህዝቡን ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም ጠንካራ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በቀጣይ መሠረታዊ የግብርና ምርቶች በስፋትና በጥራት እንዲቀርቡ በማድረግና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነት ለመቀነስ  እንደሚሠራም  ገልጸዋል።

   በክልሉ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ሥራ አጦችን በመለየትና ደረጃ በደረጃ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ውጤት ማስገኘቱን አስታውቀዋል።

በዚህም በመሠረታዊነት በግብርናና በቱሪዝም ዘርፎች ለማሰማራት የወጣቱን ክህሎትና ዕውቀት በማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ በበኩላቸው የኑሮ ውድነት ችግር ለመቀነስ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በመሰራቱ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።


 

የግብርና ምርቶች በስፋት በማቅረብ፣ አርሶ አደሮች፣ አልሚ ባለሀብቶችንና ማህበራትን በማስተሳሰርና አማራጭ የገበያ ዕድሎችን በመፍጠር የዋጋ ንረቱ እንዲረግብ መደረጉን ገልጸዋል።

በምርት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ የሚገኙ 40 ህገ-ወጥ ኬላዎችን በማስወገድ፣ 253 ህገ-ወጥ ደላሎችን ከሰብልና ከእንስሳት ግብይት ማስወጣት እንደተቻለ ሃላፊው አስታውቀዋል።

በክልሉ 67 የሰንበት ገበያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን የገለጹት አቶ ገሌቦ፣ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት በማምረታቸው ገበያው መረጋጋት አሳይቷል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት  በሥራ አጥነት ከተለዩ 250 ሺህ ዜጎች መካከል ለ112 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በለጠ ሙኒኤ ናቸው።

ከነዚህም መካከል ከ21 ሺህ የሚልቁ ወጣቶች የውጭ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በቀጣይ ወጣቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ክህሎት መር ስልጠና በመስጠት ብቁ ዜጎችን ለማፍራት እንደሚሠራም አቶ በለጠ ገልጸዋል።

  የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው የሚፈጠረው የሥራ ዕድል በዕውቀትና ክህሎት ታግዞ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ  እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቢሮው በዘርፉ የሚስተዋሉ የዕውቀትና የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሥራ ስምሪት የሚበቁ ወጣቶችን በመፍጠር ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

      ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የክልሉና የዞኖች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም