በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል- አቶ እንደሻው ጣሰው

80

ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአካል ጉዳተኞችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተከብሯል።

አቶ እንዳሻው በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ የሁሉም ዜጎች ቅንጅታዊ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በጽናት ከመቋቋም ባለፈ ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ትኩረት መስጠቱን የገለጹት አቶ እንዳሻው፣ አካል ጉዳተኞችም ፈተናን ተቋቁመው ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት መሳለጥ ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በክልሉ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን አቅምና እውቀት ተጠቅመው ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል።

ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ራሳቸውን ማብቃትና ፈተናዎችን በ"ይቻላል" መንፈስ ለማለፍ ተግተው እንዲሰሩ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

አካል ጉዳተኞችን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎምባ ደምሴ ናቸው።

የአካል ጉዳተኞችን ሰርቶ የመለወጥ ዕሳቤን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት የማበልጸጊያ ማዕከል ለማስገንባትም እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል።   

"ሁለንተናዊ ልማት የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥን ይጠይቃል" ያሉት ኃላፊው፣ በዚህ ረገድ በክልሉ ያለው ሁኔታ አበረታች ነው ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች ለመብቶቻቸው መከበር ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ሎምባ፣ የልማት ተሳትፏቸውን ለማጠናከርም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል። 

የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ ሼይቾ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል። 

የክልሉ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች እያደረገ ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት ፕሬዚዳንቱ፣ በክልሉ ለሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በዓሉን በድምቀት  ለማክበር አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ፕሬዚዳንቱ አመስግነዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለአካል ጉዳተኞች የእጅ ድጋፍ ክራንች እና የዊልቸር ድጋፍ ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም