በኢትዮጵያ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጡ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስራዎችን የሚያጎለብቱ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው

165

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስራዎችን የሚያጎለብቱ የአሰራር ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ። 

በኢትዮጵያ ጠንካራ ብሔራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አስተዳደርን መገንባት የሚያስችሉ የአዋጅ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በአለም ለ24ኛ በኢትዮጵያ ለ22ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ቀን በሳይንስ ሙዚየም አክብሯል።

ቀኑ ''አዕምሯዊ ንብረት ለዘላቂ ልማት መጪው ጊዜያችንን በኢኖቬሽንና ፈጠራ መገንባት'' በሚል መሪ ሃሳብ በፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይና በፓናል ውይይት ነው የተከበረው። 

የፈጠራ አውደ ርዕዩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር)፣ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እንዲሁም የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል ከፍተውታል። 

በዚህ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራች ሲሆን በአንዳንድ ዘርፎች የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። 

ከዚህ ቀደም የፈጠራ ስራ ባለቤቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚገድቧቸው የህግ ማዕቀፍና ፋይናንስን የመሳሰሉ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።

ይህም የፈጠራ ስራዎች እንዳይበራከቱና ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዳያበረክት ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በአገሪቱ ለፈጠራ ስራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የህግ ማዕቀፍ ከማሻሻያ ጀምሮ ለስታርት አፖች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

መንግስት ስታርት አፖች ለሀገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር ሆነው እንዲዘልቁ ብሎም ፈጠራና አዳዲስ ግኝቶች የሚያፈልቅባቸው የጥራት ማዕከል እንዲሆኑ በትጋት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል መንግስት ጠንካራ ብሄራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አስተዳደር ለመገንባት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 


 

በፍጥነት በሚለዋወጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሁኔታ በመኖሩ ቀጣይነት ያለው የለውጥ ስራ ማከናወን ይጠይቃል ነው ያሉት። 

ባለስልጣኑ ይህን በመገንዘብ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የስትራቴጂና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችና ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።

ዋና ዳይሬክተሩ  በአሁኑ ወቅት ሶስት አዋጆችን የማሻሻል እንዲሁም ሁለት አዳዲስ አዋጆችን እየተረቀቁ መሆኑን  ተናግረዋል።

ዘርፉ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችል ቢሆንም እስካሁን ባለው ሁኔታ ብዙ እንዳልተሰራበት ነው የገለፁት።

አሁን ላይ በስታርት አፕ ዙሪያ የተጀመረው ስራ የህብረተሰብ ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ሃሳቦች ተግባር ላይ እንዲውሉ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናና የአለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ስትቀላቀል ተወዳዳሪ ሆና እንድትቀጥል የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስራዎች መበራከት አለባቸው ብለዋል። 

ባለስልጣኑ የሚሰራባቸውን ህጎች ከዘመኑ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ ለማድረግ የአሰራር ማሻሻያ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። 

በአውደርዕዩ የፈጠራ ስራቸውን ይዘው የቀረቡ የፈጠራ ባለቤቶች በበኩላቸው የአዕምሯዊ ንብረት ከፈጠራ ባለቤቱ ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል። 


 

መጸዳጃ ቤትን በንፅህና ለመጠበቅ የሚያስችልና ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻን መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዘው የቀረቡት በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰበ ጤና አጠባበቅ መምህር ዶክተር ግዛቸው አብደታ እንዳሉት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና አለው። 


 

መምህር በሌለበት ጊዜ ማስተማር የምትችል ሮቦት ይዞ የቀረበው ወጣት በረከት ጌቱ በበኩሉ የፈጠራ ባለቤትነት መብት መሰጠቱ የፈጠራ ባለቤትነት ደህንነትን ከማስጠበቅ ባሻገር ስራን በማሻሻል አገርን ለመደገፍ ያግዛል ብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም