ፒያሳን የቱሪስት መስህብ የሚያደርግ የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

70

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ ፒያሳን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ትልቅ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የሚያስችል የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን  ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማትና የአድዋ ዙሪያ መልሶ ማልማት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት አራት ኪሎና ፒያሳ በርካታ ቅርሶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ያነሱት ከንቲባዋ የአካባቢውን የቱሪዝም መስህብ ለመጨመር በኮሪደር ልማቱ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም በኮሪደር ልማቱ በመታገዝ አካባቢዎቹን በመሰረተ ልማት፣ በመጋቢና ሰፋፊ መንገዶች ለማገናኘት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አካባቢው የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአጼ ምኒሊክና አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት፣ማዘጋጃ ቤትና ሌሎች ጥንታዊና ታሪካዊ ቦታዎች የሚገኙበት በመሆኑ ሃብቱን መጠቀም በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ የመጀመሪያው ሆቴል፣ ቲያትርና ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች የሚገኙበት በመሆኑ ለቱሪስቶች አመቺ በሚሆን መልኩ ለማስተሳሰር እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአገር ውስጥም ይሁን ለውጪ ጎብኝዎች የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት ግብአቶችን በሚያሰፋ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የአደጉ አገሮች ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን በማልማትና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር እየተጠቀሙበት መሆኑን በመጥቀስ በአዲስ አበባም በዚህ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከንቲባዋ በከተማዋ እየተካሄደ ባለው ልማት "ለኢትዮጵያ ትልልቅ ቅርስ እየጨመርን እንጂ ቅርስ እያጠፋን አይደለም" ብለዋል።

በመሆኑም ለቅርስ ጥበቃ፣ እድሳትና እንክብካቤ ማድረግ ለቱሪስት መስህብነትና ለታሪክ መጉላት አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት።

የኮሪደር ልማትን ከማገናኘት በተጨማሪ ለህዝብ መዝናኛ፣ ለአውቶቡስና ታክሲ ተርሚናል የሚውል 60 ሔክታር መሬት መጽዳቱን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም