በክልሉ ከ5 ሺህ 500 ለሚበልጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና እየተሰጠ ነው

96

ዲላ  ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ5 ሺህ 500 ለሚበልጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና እየተሰጠ መሆኑን  የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በዚህ ወቅት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ዳይሬክተርና የዲላ ማዕከል የፈተና አስተባባሪ አቶ ናታን ላብሶ እንደገለጹት፣ በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።

ለመምህራንና የትምህርት አመራሮች ዛሬ መሰጠት የተጀመረው የሙያ ብቃት ምዘና የዚሁ አካል መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ምዘናው በክልሉ በሚገኙ 12 የዞን ከተሞች የተጀመረ ሲሆን፣ በዚህም 5ሺህ 559 መምህራንና የዘርፉ አመራሮች ይመዘናሉ።

በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተው ምዘና በማስተማር ላይ ለሚገኙ መምህራን የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል።

መምህራንና የዘርፉ አመራሮች ለፈተናው ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡም አቶ ናታን አሳስበዋል።

የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍለ በበኩላቸው በምዘና ሥርዓቱ በዞኑ በ1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እያገለገሉ ያሉ 402 መምህራንና የትምህርት አመራሮች ዛሬ መፈተን ጀምረዋል ብለዋል ።

ምዘናው ብቃት ያላቸውን መምህራን ወደፊት በማምጣት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።

በተጨማሪም የመምህራንን ጥቅማ ጥቅምና ሙያ ከማሻሻል ባለፈ ትውልዱን በስነ ምግባርና በእውቀት ለማነጽ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም