የአደጋ ስጋት አመራርን በተደራጀና በተናበበ አግባብ መምራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወነ ነው

82

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ የአደጋ ስጋት አመራርን በተደራጀና በተናበበ አግባብ መምራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን የአደጋ ሥጋት  አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የአመራርና ሰራተኞች የቅድመ ስራ ስምሪት ስልጠና በአፍሪካ ልህቀት ማእከል ጀምረዋል።


 

ስልጠናው "በሪፎርም በተቀናጀ ፣ በተናበበና በተደራጀ አመራር ለአደጋ የማይበገር አገርና ማህበረሰብ መፍጠር" በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ያለው።

የስልጠናው አላማ የኮሚሽኑ አመራሮች እና ሰራተኞች ተመሳሳይ እሳቤ እና አረዳድ እንዲኖር የማነሳሳት እና የማብቃት መሆኑ ተመላክቷል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኮሚሽኑ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ነው።

 ከ 2005 ጀምሮ ሲያገለግል የነበረውን ፖሊሲ ማሻሻል የመጀመሪያ ስራ ተደርጎ መወሰዱን ገልጸዋል።

በዚህም ፖሊሲው አዳዲስ እሳቤዎችን አካቶ በወርሀ የካቲት አጋማሽ በሚኒስትሮች ምክርቤት ጸድቆ ወደስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

ተቋማዊ አደረጃጀትን የመፈተሽ እና የመከለስ እንዲሁም የሰው ሀይሉን እንደ አዲስ በመዋቅር  የሰው ሀይል የማጠናከር ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት አመራርን በተደራጀ እና በተናበበ መንገድ መምራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።

በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ የነበሩ ስብራቶችን የሚጠግን መሆኑን አብራርተዋል።

ፖሊሲው የሰብአዊ ድጋፍን በራስ የመሸፈን አቅምን የሚያጎለብትና ቅጽበታዊ  ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ማንኛውንም አካል ድጋፍ ሳይጠይቅ በራስ አቅም መመለስ የሚቻልበትን ሁኔታ  የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

አደጋ ልማት ባለበት እንዲቆም የሚያደርግና  ወደ ኋላም የሚመልስ በመሆኑ በአግባቡ ተረድቶ መምራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ፖሊሲው የልማት እቅድ አካል  መሆኑን ገልጸው ከልማት እና እድገት እቅድ ጋር የሚተገበር መሆኑን ጠቁመዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀን 16/06/2016 ዓ.ም የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲን ማጽደቁ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም