በከተማዋ የኮሪደር ልማት ለግል ይዞታ ተነሺዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል

82

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት ለግል ይዞታ ተነሺዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መከፈሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አኳሂዷል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማትና የአድዋ ዙሪያ መልሶ ማልማት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ከንቲባዋ በሪፖርታቸው የኮሪደር ልማት ለከተማዋና ለነዋሪዎቿ ያለውን ፋይዳ፣ የትግበራ ሂደት፣ የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል።

በትግበራ ሂደቱ መኖሪያ ቤት ማስተላለፍ፣ ለንግድ ቤቶችና ለግል ባለይዞታዎች ምትክ መሬትና የካሳ ክፍያዎችን በመፈጸም የተከናወኑ ተግባራትን ዝርዝረዋል።

በዚህም ለ307 የግል ይዞታ ተነሺዎች 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ለመፈጸም መወሰኑንና እስካሁን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ለ417 የቀበሌ ንግድ ቤቶች እና ለ393 የፌደራል ኪራይ ቤቶች ባለይዞታዎች 30 ሄክታር ምትክ መሬት ተዘጋጅቶ እየተስተናገዱ መሆኑን አመላክተዋል።

የከተማ ፕላን መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የመብራት፣ ቴሌኮም፣ የደህንነት መጠበቂያ ካሜራ በመሬት ውስጥ እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከተማዋን ከድንገተኛና ሰው ሰራሽ የተፈጥሮ አደጋዎች ለመታደግ ያግዛል ብለዋል።

እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ማህበራዊ ችግርን በመፍታት፣ የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ፣ ዘመናዊ ከተማን እውን ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት አንስተዋል።

በትግበራው የልማት ተነሺዎች ተገቢውን ቦታና ካሳ እንዲያገኙና ቅርሶች እንዲጠበቁ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

የስራ ትስስር፣ ለተነሺዎች ያልተሟሉ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የታጠሩ ቦታዎች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ክትትል ማድረግ ፣ በኮሪደር ልማቱ የታየው የስራ ባህል እንዲቀጥል ማድረግ በቀጣይ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠቁመዋል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽ በመስጠት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ በዛሬ መደበኛ ጉባኤው ለከተማ አስተዳደሩ ለ2016 በጀት አመት ተጨማሪ 21 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ያጸደቀ ሲሆን በአባላት ስነ-ምግባር ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም