ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአካል ጉዳተኞችን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት ተከናውነዋል

71

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአካል ጉዳተኞችን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ገለፀ።

የሰው ልጆች በተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ መንስኤዎች የአካል ጉዳት ሊገጥማቸው ይችላል ።

አካል ጉዳተኞች ያጋጠማቸው ችግር ሳይበግራቸው ምርታማ ሆነው ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ሀገራቸውን ለማገልገል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ይገጥማቸዋል።

አካል ጉዳተኞች ለረጅም ዘመናት ከሚያነሷቸው ችግሮች መካከል በሀገሪቱ በሚፈለገው ደረጃ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መሰረተ ልማቶች አለመኖር ይጠቀሳል።

ይህን ተከትሎ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ፌደሬሽኑ አካል ጉዳተኞች የሚያነሷቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከተለያዩ ባለድርሻ እና አጋር  አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በባለፉት የለውጥ ዓመታት የአካል ጉዳተኞችን የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል ።

በሀገሪቱ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች በአብዛኛው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ላለመሆናቸው ምክንያቱ የተቋማት በቅንጅት የመስራት ልምድ ሳይጎለብት በመቆየቱ እንደሆነ አንስተዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ችግሩ እየተቀረፈ በመምጣቱ ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የአካል ጉዳተኞችን የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ስምምነቶች ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በለውጡ ዓመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞች የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም አሁንም አካል ጉዳተኛው ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች አንጻር በርካታ የቤት ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

መንግስት የሚሰራቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ለጀመረው ስራ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ማሳያ መሆኑን በአብነት አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር የጀመራቸው ስራዎችም የአካል ጉዳተኛውን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አቶ አባይነህ አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም