በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስገኘ መሆኑ ተገለጸ

69

ደሴ፤ ሚያዝያ 18 /2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  ምቹ ሁኔታ በመፍጠር   ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን ገለጹ።   

የክልልና የዞን አመራር አባላት በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የሌማት ትሩፋት ስራዎች እንቅስቃሴን  ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ የከተማው ነዋሪ በአነስተኛ ስፍራ ዶሮ፣ ወተት፣ ማር፣ ዓሳና ስጋ አምርቶ ከመመገብ ባለፈ ምርት ለገበያ በማቅረብ ተስፋ ሰጪና አበረታች ውጤት እያስገኘ  መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ለማጠናከር  ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፤ በህብረተሰቡ የለሙ ተፋሰሶችም ለሌማት ትሩፋት ስራ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት የዜጎችን ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የዞኑን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እያገዘ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ናቸው።

በዚህም ህብረተሰቡ በትንሽ ስፍራ የእንስሳት ተዋጽኦን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ እያመረተ ተጠቃሚ እንዲሆን ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም