በሀገር ደረጃ 57 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩቶች ተሰራጭተዋል - ግብርና ሚኒስቴር

77

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 18/2016 (ኢዜአ):-በሀገር ደረጃ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ57 ሚሊዮን በላይ የዶሮ ጫጩቶች መሰራጨታቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንደገለጹት፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው።   

መርሃ ግብሩ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በሀገር ደረጃ የሚሰራጩት የዶሮ ጫጩቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት የሚሰራጩት የዶሮ ጫጩቶች መጠን በዓመት ከ20 ሚሊዮን ያልዘለለ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከመርሃ ግብሩ በኋላ ባለፈው ዓመት ቁጥሩ ወደ 42 ሚሊዮን ማደጉን ጠቁመው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 57 ሚሊዮን ጫጩቶች በሀገር ደረጃ ተሰራጭቷል ብለዋል።


 

ከእንቁላል ምርትና ምርታማነት አኳያም አመርቂ ዕድገት እየታየ መሆኑን ነው ዶክተር ፍቅሩ የገለጹት።

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ከ6 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ እንቁላል ለማምረት ታቅዶ በዘጠኝ ወራት 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን እንቁላል ማምረት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የሥነ ምግብ ባለሙያ ዶክተር አንተነህ ኡመር በበኩላቸው እንዳሉት እንደ ሀገር በተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተከናወነ ያለው የዶሮ ልማት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕፃን እንቁላል እየተመገበ የሚያድግበት ይሆናል። 


 

በኢትዮጵያ ከ10 ሕፃናት አራቱ የእንስሳት ተዋጽኦና ሌሎች የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ለመቀንጨር ችግር ይጋለጣሉ።

እንቁላል በአግባቡ የተመገቡ ሕፃናት ካልተመገቡት ጋር ሲነጻጸሩ ለመቀንጨር ችግር የመጋለጥ እድላቸው በተወሰነ ደረጃ ቀንሶ መገኘቱንም ባለሙያው አመልክተዋል።

ዶክተር አንተነህ እንዳሉት የተመጣጠነ ምግብ ለሕፃናት መመገብ የነገውን ትውልድ ንቁና ብቁ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

እንደ ሀገር በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተመዘገበ ያለው ውጤት ትርጉሙ ብዙ ነው ያሉት ዶክተር አንተነህ፣ መርሃ ግብሩ የቀጣይ ትውልድ ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ በተለይ በገጠር ዶሮን በስፋትና በጥራት የማርባት ልምድ ባለመኖሩ የቤተሰብ ተጠቃሚነት እምብዛም  እንደሆነ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በቤተሰብ ደረጃ ዶሮን በብዛት የማርባት ባህል እየተለመደ መምጣቱ ለሌማትም ለገበያም የሚሆን እንቁላል ለማግኘት እያስቻለ ነው ብለዋል ባለሙያው።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ሉአላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የተመጣጠነ ምግብ በቤተሰብ ደረጃ ለማሟላትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑ ይገለጻል።

የመርሃ ግብሩን የአንድ ዓመት ተኩል አፈጻጸም የገመገመ ሀገራዊ መድረክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድር እና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም