የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን ከፍጻሜ ለማድረስ ርብርብ እንደሚደረግ ተገለጸ

78

ጎንደር፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ ርብርብ እንደሚደረግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት የግድቡን የስራ እንቅስቃሴ ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ ከፍተኛ በጀት ተይዞለት የተጀመረ የልማት ፕሮጀክት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ከአካባቢው መልክዓ ምድር አቀማመጥ አስቸጋሪነት ጀምሮ የግንባታ አቅርቦትና የፋይናንስ እጥረት እንዲሁም በተቋራጮች የአቅም ማነስና ተነሳሽነት ችግሮች ሳቢያ መጓተቶች አጋጥሞት መቆየቱን አውስተዋል፡፡

አሁን ላይ የግንባታው አፈጻጸም 68 በመቶ የደረሰ ሲሆን በተለይ የጎንደር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት በመፍታት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ያጋጠሙትን ማነቆዎች በዝርዝር በመፈተሽ የክልሉና የፌዴራል መንግስት በተናጠልና በጋራ የድርሻቸውን የሚወጡበትን አሰራር እንደሚዘረጋም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ፕሮጀክቱን ለፍጻሜ ለማብቃት በጋራ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር በኢንቨስትመንትና በመሰረተ ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎችም አበረታች መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

የአመራር አባላቱ ጉብኝት በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ የፌዴራል የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ እንዲበቁ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው፡፡

እንዲሁም በከተማው በፌዴራል መንግስት ተጀምረው የተጓተቱ የአዘዞ ቡልኮ የኮንክሪት አስፋልት መንገድና የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክቶች ችግሮቻቸው ተፈትቶ ለፍጻሜ እንዲበቁ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን ጨምሮ የክልልና ከተማ አስተዳደሩ የአመራር አባላት የተሳተፉ ሲሆን፤ በከተማው እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም