በክልሉ ኢንተርፕራይዞች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር አለበት -ምክር ቤቱ

70

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች በሙሉ አቅማቸው ማምረት እንዲችሉ የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት የክልሉ ምክር ቤት አሳሰበ።

በክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ የተመራ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በአርባ ምንጭ ከተማ የኢንተርፕራይዞችን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

በዚህን ጊዜ በክልሉ ምክር ቤት የፕላን፣ መሠረተ ልማትና የመንግሥት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕንቁ ዮሐንስ እንዳስገነዘቡት ኢንተርፕራይዞችን ማበረታታትና መደገፍ ያስፈልጋል።


 

ክልሉ ኢንተርፕራይዞች ጎልተው መውጣት እንዲችሉ በሁሉም ዘርፍ የጀመረው ድጋፍ በተቀናጀ መንገድ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለይ ኮርፖሬሽኑ የኢንተርፕራይዞችን አቅም በማሳደግ በክልሉ ያለው የግብርና ምርት እሴት ተጨምሮበት በጥራትና በብዛት ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ ኢንተርፕራይዞቹ በሙሉ አቅማቸው በማምረት የውጭ ምንዛሬ በማዳንና በሥራ ዕድል ፈጠራ የድርሻቸውን እንዲወጡ  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ዕንቁ፣ የኢንዱስትሪዎች ማደግ የኢኮኖሚ ችግርን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።  

የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ለኢዜአ እንዳሉት፣ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች 114 አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ወጪና ተኪ ምርቶችን በማምረት የድርሻውን እየተወጡ ነው ብለዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወጪ ምርት ከ700 ሺህ በላይ ዶላር፣ ከተኪ ምርቶች ደግሞ 38 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ነው የጠቀሱት።

ኢንተርፕራይዞቹ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ሺህ 200 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

አቶ ጥላሁን እንዳሉት በክልሉ የሚገኙት የተቀናጀ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በኢኮኖሚና በሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጿቸው እንዲያድግ መሰረተ ልማት ከማሟላት ጀምሮ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

በአርባ ምንጭ ከተማ የ”ጃኖ ዕደ-ጥበብ” ኢንተርፕራይዝ ባለቤት ወጣት ፍሬው ቆንጆ የእጅ ሥራ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ በብዛት ባለመኖራቸው ይህን ዕድል ለመጠቀም ወደ ሥራው መግባቱን ገልጿል።


 

በዚህም ለቤት ውስጥና ለፋሽን የሚሆን የዕደ-ጥበብ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ከማቅረብ ባለፈ በአሜሪካና በአውሮፓ ገበያዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ነው የተናገረው።

''የአባቶችን የዕደ-ጥበብ አሠራር ባህል ወደ አሁኑ ትውልድ እያስተላለፍን እንገኛለን'' ያለው ወጣቱ፣ ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት ለ80 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።

በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው ”ያላ ወተት ማቀነባበሪያ” ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለማየሁ እሥራኤል በፋብሪካው ቺዝ፣ ክሬም፣ ቅቤ፣ እርጎና ወተት በማምረት ላይ ናቸው።


 

ፋብሪካው በጋሞ ዞን ሁሉም ወረዳዎችና አጎራባች ዞኖች የወተት ማሰባሰቢያ ማዕከላት በማቋቋም ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

ፋብሪካው ከሁለት ወራት በኋላ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሲገባ በወተት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን እጥረት በማቃለል የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት የድርሻውን እንደሚወጣ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም