በክልሉ ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትኩረት ይሰጣል---አቶ እንዳሻው ጣሰው

72

ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 18/2016 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማብቃትና የመደገፍ ሥራ ይሰራል ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት የአካል ጉዳተኞች የእኩል ተጠቃሚነት መብት እንዲረጋገጥ በክልሉ በተቀናጀ መንገድ ይሰራል።

በክልሉ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነው ራሳቸውን ከማስተዳደር ባለፈ ለሌሎች እንዲተርፉ የማብቃትና የመደገፍ ሥራ ይሰራል። 

ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ በክህሎት በማብቃት በኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ቅንጅታዊ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።


 

የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎምባ ደምሴ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተደነገጉ ህጎች እንዲተገበሩ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

አካል ጉዳተኞች በተለያየ መንገድ ክህሎታቸውን በማውጣት እንዲያዳብሩ የሚያግዝ ማበልጸጊያ ማዕከል ክልሉ በማስገንባት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ቢሮው ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የአካል ጉዳተኞት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚያግዙ ሥራዎች ላይ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።   

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ በክልሉ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም