ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በሆነው "ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ" አባል ለመሆን እየሰራች ነው

66

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በሆነው "ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ" አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ በተለያዩ ጉዳዮቾ ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመዲናችን በቅርቡ ጉብኝት ያደረጉት የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ታዬ አጽቀስላሴ ጋር ተገናኝተው በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጉዳዮችን መምከራቸውን ተናግረዋል። 

የፊታችን ሀምሌ ወር ኢትዮጵያ 4ኛውን የፋይናንስ ለልማት ኮንፍረንስ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ገልጸው፤  ለዚሁ ስራ ከመንግስታቱ ድርጅትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር  እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ምክክር መደረጉን ገልፀዋል። 

የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበረም ነው የተናገሩት፡፡

የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር አገራቱ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸውንም አንስተዋል።

በሩስያ ሞስኮ ከተማ በተደረገው የብሪክስ አባል ሀገራት ምክክር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ መሳተፉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል የሆነችው ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቷን ለማሳካት መሆኑንም አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ የብሪክስ አባል አገራት ተሳትፎ መገምገሙንና ለቀጣይ የቡድኑ ስብሰባ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በሆነው "ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ" አባል እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በስብሰባው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ምክክር መደረጉን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ልዑክ ከአባል ሀገራት ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ምክክር መደረጉን ገልፀዋል።

 

 
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም