በአማራ ክልል በመስኖ ልማት የተገኘው ምርት ገበያውን  እያረጋጋ ነው 

53

ደሴ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ልማት የተገኘው  ምርት ገበያውን  ከማረጋጋት ባለፈ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተግባር እያሳየ መሆኑን  በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ።  

የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት በቃሉ ወረዳ የመስኖ ልማትና የፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያ ጎብኝተዋል፡፡

 ዶክተር ድረስ ሳህሉ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ ሀብት በመጠቀም የበጋ መስኖ ልማት አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም የምግብ አቅርቦት ክፍተቱን ከመሙላት ባለፈ ምርት በብዛት ለገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ግብ ተይዞ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው የበጋ ወራትም በሁለት ዙር 333 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን በተደረገ ጥረት ከ293 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ምርት ደርሶ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው፤ ምርቱ ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተቃሚነት በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው፤ በክልሉ በመጀመሪያው ዙር በበጋ መስኖ ከለማው መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል ብለዋል፡፡

ይህም ይስተዋል የነበረውን የምርት አቅርቦት እጥረት በማቃለል የገበያ ዋጋ እንዲረጋጋ ሰፊ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የምርት ስብሰባና የሁለተኛ ዙር መስኖ ልማት ስራ እንቅስቃሴ በተጠናከረ አግባብ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የቃሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን አህመድ ፤ በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከ3 ሺህ 500 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የለማው ቲማቲም፣ ሽንኩርት፤ ቃሪያ፣ ድንችና ሌሎች የደረሰ ምርት መሰብሰቡን አመልክተው፤  ምርቱ የገበያ ዋጋ በማረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን  ተናግረዋል።

በበጋ መስኖ ልማት ያገኙት ምርት ከፍጆታቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በቃሉ ወረዳ የ01 ቀበሌ  አርሶ አደር አወል ይማም ናቸው፡፡

ግማሽ ሄክታር መሬት ቲማቲምና ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎችንም አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ከ50 ኩንታል በላይ ምርት ሰብስበው ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም