በአገሪቱ ጠንካራ ብሔራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አስተዳደርን መገንባት የሚያስችሉ የአዋጅ ማሻሻያዎች እየተከናወነ ነው

54

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ጠንካራ ብሔራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አስተዳደርን መገንባት የሚያስችሉ የአዋጅ ማሻሻያዎች እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በአለም ለ24ተኛ በኢትዮጵያ ለ22ተኛ የሚከበረውን የዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ቀን ''አዕምሯዊ ንብረት ለዘላቂ ልማት መጪው ጊዜያችንን በኢኖቬሽንና ፈጠራ መገንባት'' በሚል መሪ ሃሳብ  በፈጠራ ስራዎች አውደርዕይና በፓናል ውይይት እየተከበረ ይገኛል። 

የፈጠራ አውደርዕዩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር )፣ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር ) እንዲሁም የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል ከፍተውታል። 

በዚህ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር ) እንዳሉት ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራች ሲሆን በአንዳንድ ዘርፎች የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። 

መንግስት ስታርትአፖች ለሀገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር ሆነው እንዲዘልቁ ብሎም ፈጠራና አዳዲስ ግኝቶች የሚያፈልቁበት  የጥራት ማዕከል እንዲሆኑ በትጋት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል መንግስት ጠንካራ ብሄራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አስተዳደር ለመገንባት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 

በፍጥነት በሚለዋወጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሁኔታ የሚተገበር በመሆኑ ቀጣይነት ያለው የለውጥ ስራ ማከናወን ይጠይቃል ነው ያሉት። 

ባለስልጣኑ ይህን በመገንዘብ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የስትራቴጂና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችና ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ  በአሁኑ ወቅት  ሶስት አዋጆችን የማሻሻል እንዲሁም ሁለት አዳዲስ አዋጆችን እየተረቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም