ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አዲስ ተግባር እና ንቅናቄ ይፋ አደረጉ

53

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ክብር ያለው የንጽሕና ባህልን ለማዳበር ያለመ አዲስ ተግባር እና ንቅናቄ ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትርሩ ንቅናቄውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ንቅናቄውን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።

ንቅናቄው የመጸዳጃ ቤቶችን ተደራሽ ማድረግና ክብርን ጠብቆ የመጸዳዳት ባህልን ለማዳበር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። 

ክብር ያለው የንጽሕና ባህል ማለት በተገቢው ቦታ ክብርን ጠብቆ መጸዳዳት ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚያ ደግሞ ስርዓት ማበጀትና የመጸዳጃ ቦታ መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል።
 

ስርዓቱን በተመለከተ በማስተማርና ህግ በማስከበር ልናመጣው፣ ልናሳድገው እንችላለን ያሉ ሲሆን ቦታውን ደግሞ መገንባት ይጠበቅብናል የግንባታውም ተግባር ዛሬ መጀመር እንዳለበትም ተናግረዋል።

ንቅናቄው የስራ እድል የሚፈጥርና ጤናን ለመጠበቅ በእጅጉ የሚያግዝ እና የኑሮ ዘዬን የሚያዳብር መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመልካም ተግባር ላይ የምትሳተፉ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ከተማችንን ጽዱ አረንጓዴና ውብ ለማድረግ ከጎናችን እንደምትቆሙ ሙሉ እምነት አለን ብለዋል።

“በዚህም በከተማዋ በርከት ያሉ የመጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት ባለን መሻት የዚህ አላማና ሀሳብ ተጋሪ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች በገንዘብ አልያም መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ከጎናችን እንድትሆኑ እየጠየኩ በተባበረ ክንድ ከተማችንን እናስውብ እናጽዳ የኑሮ ዘያችንን እንቀይር” ሲሉም መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ ጽዱና አረንጓዴ ከባቢን መፍጠር መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክብር ያለው የንጽሕና ባህል መፍጠር ይኖርብናል ብለዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም