ቀጥታ፡

በከተማው እየተከናወነ  ያለው የኮሪደር ልማት የመጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገና ከተማዋን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተገነባ መሆኑን  የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ ።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 3ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል ።

በጉባኤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማው እየተካሄዱ ያሉ የልማት ስራዎችን በተለይ የኮሪደር ልማትን የ45 ቀናት አፈጻጸም የተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል።

በዚህም መጪውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማትና የመልሶ ማልማት ስራዎች ጥራትና ፍጥነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምርጫ ወቅት አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ ለማድረግ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ  እንድትሆን ለመስራት ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን አቅዶ በመስራት እና ነባሮቹን በማደስ ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ከተማዋ ካለባት የመሰረተ ልማት እጥረት እና የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ እንዲሁም ዘመናት ያስቆጠሩ መሰረተ ልማቶችን ለማዘመን፣ ለማደስ እና የነዋሪዎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የኮሪደር ልማት ማከናወን መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያነቷን የሚመጥን ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ ውስጥም የኮሪደር ልማቱ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

በ5ቱም የኮሪደር ልማት፣  5 ሺህ 135  ቤቶች  በማንሳት ቦታውን አፅድቶ ለልማት ዝግጁ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።


 

እስካሁን 80 በመቶ በላይ  የልማት ተነሺዎች ካሳ፣ ምትክ ቦታ፣ ምትክ ቤትና ምትክ መስሪያ ቦታ በመስጠት እንዲስተናገዱ ተደርጓል፡፡

በኮሪደር ልማትና በመልሶ ማልማት የሚነሱ የከተማችን ነዋሪዎችም የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ ምትክ መሬት፣ ካሣ፣ የመስሪያ ቦታ፣ ሼዶች፣ የትራንስፖርት ወጪ፣ የሞራል ካሣ እንደተሰጣቸው ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በቦታቸው በኮሪደር ልማቱ ጥናት መሰረት ማልማት ለሚችሉ መልሶ የማልማት መብት ተጠብቆላቸው እና ለግል የመኖሪያ ቤት ተነሺዎች መኖሪያ ቤት እስከሚገነቡ የቤት ኪራይ ወጪ ጭምር እንዲያገኙ በማድረግ የተተገበረ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱን 24 ሰዓት በመስራት በሶስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ አሁን ላይ ለ1 ሺ 485 ዜጎች ቋሚና ለ13 ሺ 784 ዜጎች ጊዜያዊ በድምሩ ለ15 ሺ 269 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ግንባታው ሲጠናቀቅ አሁን ከፈጠረው የስራ ዕድል 51 በመቶ ከፍ ያለ ተጨማሪ የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡

ይህ የልማት ስራ በትብብር፣ በቅንጅትና በመናበብ፣ በፍጥነትና በጥራት እየተሰራ ሲሆን ይህም ለአገሪቱ አዲስ የስራ ባሀል ፈጥሯል ነው ያሉት።

አዲስ አበባ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየተሰራ ያለውን ስራ ከሃሳብ አመንጪነት እስከ ድጋፍና ክትትል ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

በኮሪደር ልማቱ የሚገጠሙ ችግሮችና የተሳሳቱ መረጃዎችን በፍጥነት በማረምና  ህብረተሰቡ እውነታውን ተረድቶ ልማቱን እንዲያግዝ የተሄደበት ርቀት የሚመሰገን ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም