በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና እየተሸጋገረች መሆኗን ማረጋገጫ ናቸው- የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ

94

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና እየተሸጋገረች እንደምትገኝ ማረጋገጫ መሆናቸውን የከተማዋ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና ጥራት እንዲከናወኑ ምክር ቤቱ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችን እና በልማቱ የተነሱ ነዋሪዎች በተዘጋጁላቸው ምትክ መኖሪያ መንደሮች ተገኝተው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቃድርን ጨምሮ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ አባላት እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ እንዳሉት፤ የምክር ቤቱ አባላት የህዝብ ወኪል በመሆናቸው የመዲናዋ የልማት ስራዎችን የመከታተልና ጉድለቶችን የመገምገም ግዴታ አለባቸው።

በዛሬው ዕለትም የኮሪደር ልማት ስራዎች እና በኮሪደር ልማቱ ተነስተው በአቃቂ ቃሊቲ፣ በሃና ፉሪ እና ጉራራ  ምትክ የጋራ መኖሪያ ቤት የተሰጣቸው ነዋሪዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።


 

ምክትል አፈ ጉባኤዋ አክለውም የተጀመረው የልማት ስራ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ ምክር ቤቱ የክትትል እና ድጋፍ ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ፣ ውብና ጽዱ አደርጎ የማዘመን እንዲሁም ከዓለም ከተሞች ተወዳዳሪና ተመራጭ ከተማ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና እየተራመደች መሆኗን ሁነኛ ማረጋገጫ እንደሆነም ምክትል አፈ ጉባዔዋ አብራርተዋል።

በኮሪደር ልማት ሳቢያ ተነስተው በአጭር ጊዜ ምትክ የጋራ መኖሪያ ቤት የተሰጣቸው ነዋሪዎች በልዩ ትኩረት የመሰረተ ልማት እና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲሟሉላቸው መደረጉን አረጋግጠናል ነው ያሉት። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም