ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በአማራ ክልል የሰብል ጉዳት ላጋጠማቸው አርሶ አደሮች 39 ሚሊዮን ብር  የሰብል መድን ዋስትና ሰጠ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ሰብላቸው በበሽታ ለተጎዳባቸው አርሶ አደሮች  39 ሚሊዮን ብር  የሰብል መድን ዋስትና ሰጠ።

ኢንስቲትዩቱ ለአርሶ አደሮች የሰብል መድን ዋስትና የሰጠው ከዓለም ምግብ ፕሮግራምና ፑል አድቫይዘርስ በፈጠረው ጥምረት በተቋቋመ የሰብል መድን  በኩል መሆኑ ተገልጿል።

የሰብል መድን ዋስትናው የስንዴ ሰብልን በሚያጠቃው ዋግ ሰብላቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም ያለመ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የስራ አመራር  ስራ አሰፈፃሚ ዳዊት ፊሊጶስ  የሰብል መድን ዋስትና ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የሰብል ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ በመክፈል እያቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት በአማራ ክልል በሁለት ወረዳዎች ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች 39 ሚሊዮን ብር የሰብል መድን ዋስትና መሰጠቱን ገልጸዋል።

በመድን ዋስትናው ከ50 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የሰብል መድን መክፈሉን ገልጸው፥ በቀጣይ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በሌሎችም ክልሎች እንደሚሰፋ ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ የሰብል መድን አባል በመሆንና ክፍያ በመክፈል ጉዳት ሲደርስበት የዋስትና ክፍያ እንዲከፈለው በማድረግ መልሶ እንዲቋቋም የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት  በድርቅ፣ በከባድ ዝናብ እና በተባይ በሽታ ሰብላቸው ለተጎዳባቸው ለ122 ሺህ አርሶ አደሮች የሰብል መድን ዋስትና በመስጠት ማቋቋሙን ተናግረዋል።

የሰብል መድን ዋስትና በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ በዓለም ምግብ ፕሮግራምና በፑላ አድቫይዘርስ ትብብር በግብርናው ዘርፍ  በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች ችግሮች የሚከሰትን አደጋ መፍትሔ ለመስጠት የተመሰረተ ድርጅት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም