በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል  የፋይናንስ ዘርፉን ከብክነት የጸዳ ለማድረግ እየተሰራ ነው

108

ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የልማት ዕቅዶች ጋር ሊጣጣም የሚችል የበጀት አመዳደብና አጠቃቀም ሥርዓት በመከተል የፋይናንስ ዘርፉን  ከብክነት የጸዳ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የክልሉ  ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር የሕግ ማዕቀፎችና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ነው።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ በመድረኩ እንዳሉት፤ በክልሉ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር የሕግ ማዕቀፎች ላይ  የአመራር ግንዛቤ ክፍተት ይስተዋላል።

ለዚህም በየመዋቅሩ የሚገኙ የኦዲት ግኝት ውጤቶች ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማቃለል ተከታታይነት ያለው ስልጠና ነክ የምክክር መድረክ ለአመራር አባላት ተዘጋጅቶ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

እየተካሄደ ባለው መድረክም በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር የሕግ ማዕቀፎች፣ በግዥ መመሪያና በመረጃ አያያዝ እና አጠቃቀም ሥርዓት ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።

የፋይናንስ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ እንዲቻል ቢሮው አስፈላጊ የኮምፒውተር እና ተያያዥ ግብዓቶችን ለታችኛው መዋቅር የማሟላት ሥራ ላይ ማተኮሩን ጠቁመዋል።

የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን የተከተለ የበጀት አጠቃቀም ሂደት ተግባራዊ እንዲደረግ አመራሩ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይ ከልማት ዕቅዶቻችን ጋር ሊጣጣም የሚችል የበጀት አመዳደብና አጠቃቀምን ሥርዓት በመከተል የሀብት ብክነትን ማስቀረት ላይ ትኩረት ተደርጎ  እንደሚሠራ አመላክተዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፤ በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ የፋይናንስ አጠቃቀም ግድፈቶችን ደረጃ በደረጃ ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ፋይናንስን በእውቀትና በክህሎት በመምራት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባ አመልክተው፤ የአቅም ውስንነቶችን ለመሙላት በተለያዩ ጊዜያት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ይሰጣሉ ብለዋል።

 ውስን በጀት ሚዛኑን ጠብቆ ለሕዝብ ልማት እንዲውል ለማድረግ በአግባቡ መረጃ ማደራጀት ላይ ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆይ የውይይት መድረክ  የክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና  የዞን ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም