በስነ-ተዋልዶ የጤና ችግሮች ምክንያት በአፍላ ወጣቶች ላይ የሚከሰተውን ሞትና ጉዳት መቀነስ ትኩረት ተሰጥቷል

144

ጂንካ፤ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፦ በስነ-ተዋልዶ የጤና ችግሮች ምክንያት በአፍላ ወጣቶች ላይ የሚከሰተውን ሞትና ጉዳት የመቀነስ ተግባር ትኩረት  መሰጠቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

 ሚኒስቴሩ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች በቀጣይ ሶስት  አመታት የሚተገበር በአፍላ ወጣቶችና በወጣቶች የጤና አገልግሎት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት የማብሰሪያ ፕሮግራም ዛሬ በጂንካ ከተማ አካሂዷል።

በአፍላ ወጣቶችና በወጣቶች የጤና አገልግሎት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክቱ በፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ይፋ የተደረገ ሲሆን ለትግበራ ከ192 ሚሊዮን ብር በጀት በላይ መመደቡ ታውቋል።

በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የፕሮጀክት ግራንት አስተዳደር አማካሪ አቶ ውቤ ደምሴ እንደገለጹት የአፍላ ወጣቶች ጤና ጉዳይ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ነው።


 

የጤና ሚኒስቴር የወጣቶችንና የአፍላ ወጣቶችን ጤና ለማስጠበቅና ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

በአምስት አመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲሁም በሶስት አመቱ የኢንቨስትመንት ፕላን ውስጥ በማካተት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ለዚህም የጤና አገልግሎቶች ማሻሻልና ምቹ ማድረግ የሚጠበቅ ሲሆን በ2025 ደግሞ 80 በመቶ የሚሆነው የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች አቅም በማጎልበት የአፍላ ወጣቶች የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀና ምቹ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም አሁን ላይ 13 በመቶ ላይ ያለውን አላስፈላጊ የአፍላ ወጣቶች እርግዝና እኤአ በ2030 ወደ 6 ነጥብ 5 በመቶ ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች ስለ ስነ-ተዋልዶና የጤና ችግሮች በቂ መረጃ የሚያገኙበት ''የኔ ታብ''የተሰኘ የበይነ-መረብ መተግበሪያ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን አንስተዋል።

ዛሬ የተበሰረው ፕሮጀክትም እንደ ሀገር  የአፍላ ወጣቶችና የወጣቶችን ጤና ለማጎልበትና ከውስብስብ ችግሮች ለመታደግ መንግስት ለሚሰራቸው ስራዎች አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል።

በስነ- ተዋልዶና በተያያዥ ችግሮች በአፍላ ወጣቶች ላይ የሚከሰተውን ሞት ለመታደግ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ቤዛ ፤ ወጣቶች በአዕምሮ፣ በአካልና በማህበራዊ እድገት የሚያሳዩት ለውጥ ለሀገራዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

"ወጣቶችን ለውስብስብ የጤና ችግሮች እያጋለጡ ያሉ አደንፃዥ ዕፆች፣ በፆታዊ ግንኙነት ወቅት የሚፈጠሩ ያልተፈለገ እርግዝና፣ አባላዘር፣ኤች አይ ቪ አዲስና ለመሰል ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል ።

ዛሬ የተጀመረው ፕሮጀክትም የክልሉ ጤና ቢሮ በወጣቶችና በአፍላ ወጣቶች ስነ-ተዋልዶና ጤና  ላይ ለሚሰራቸው የጤና ልማት ስራዎች አጋዥ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም