የፀጥታ ኃይሉ አቅም እየተጠናከረ በመምጣቱ የሠላም ሁኔታው መሻሻል አሳይቷል

167

 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦  የባህርዳር ጎንደር ኮማንድ ፖስት የደቡብ ጎንደር ዞን የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር  የፀጥታ ኃይሉ አቅም እየተጠናከረ በመምጣቱ የሠላም ሁኔታው መሻሻል ማሳየቱ ገለጸ።
 
በባህርዳር ጎንደር ኮማንድ ፖስት ደቡብ ጎንደር ዞን የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታውን አስመልክቶ ከከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ኃይል ጋር ውይይት አድርጓል። 

አጠቃላይ የከተማውን የፀጥታ ሁኔታና የተልዕኮ አፈፃፀም እንዲሁም የተልዕኮ አፈፃፀሙ እያስገኘ ባለው ውጤትና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ነው ውይይት ያካሄደው። 


 

በአካባቢው ተልዕኮ በመፈፀም ላይ የሚገኘው ክፍለጦር አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ኮሎኔል ሻምበል አስማማው እንደገለጹት ኮማንድ ፖስቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ የፀጥታ ኃይሎችን አቅም ማጠናከር፣ በራስ አቅም ግዳጅ መፈፀምና የቀጠናውን ሠላም ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የባህርዳር ጎንደር ኮማንድ ፖስት አስቀምጦት የነበረው የአፈፃፀም አቅጣጫ የተሻለ ነው ብለዋል።

ኮሎኔል ሻምበል አስማማው የሠራዊቱን ምት መቋቋም ተስኖት የተበተነውን ፅንፈኛ የማደን ስራ በተጠናከረ መንገድ እየፈፀመ መሆኑን ጠቁመው የፀጥታ ኃይሉ ደግሞ አካባቢውን በሚገባ በራሱ አቅም መጠበቅና ሠላሙን ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል። 


 

የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን በበኩላቸው አሁናዊ የከተማ አስተዳደሩና የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ መሻሻል የታየበት መሆኑንና የፀጥታ ኃይሉ ራሱን ችሎ አካባቢውን በንቃት ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረትም አበረታች ነው ብለዋል። 

አቶ ደሴ መኮንን ኮማንድ ፖስቱ ያስቀመጠውን የአፈፃፀም አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ አቅማችንን የበለጠ ማጠናከር ይግባናል ብለዋል። 

በዚህም  የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ሁሉም የፀጥታ ኃይል ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ እንደሚገባውም መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የከተማው የኮማንድ ፖስት አባል ሻለቃ ጭፍራው አሰፋ በበኩላቸው የከተማው ፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ ሠላም አስከባሪና የአድማ ብተና ኃይሉ ከሠራዊቱ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ የሠላም ሁኔታውም ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም