በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጥራታቸውን ያልጠበቁ መድሀኒቶች ተወግደዋል

116

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጥራታቸውን ያልጠበቁ መድሀኒቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ እንዲሁም እንዲወገዱ ማድረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የመድሃኒት ዘርፍ ምክትል ዳሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የመድሃኒት ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስትራቴጂክ ዕቅዶች አውጥቶ እየሰራ ነው።

በዚህም ከመግባቢያና መውጫ ኬላዎች ጀምሮ በመድሃኒት ዘርፍ አምራቾች፣ አስመጪና ላኪዎች ላይ ጠንካራ የቁጥጥር እና ክትትል ስራዎችን ማከናወን መቻሉን አንስተዋል።

ባለስልጣኑ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ባደረገው ቁጥጥርና ፍተሻ 61 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚገመቱ መድሃኒቶችን ጥራትና ፈዋሽነት በማረጋገጥ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ነገር ግን 132 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድሀኒቶች ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነታቸው ባለመረጋገጡ ወደ ሀገር እንዳይገቡ እና እንዲወገዱ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ291 የአገር ውስጥ አስመጪና አከፋፋይ ተቋማት ፍቃድ መሰጠቱን  ጠቁመዋል።

ፈቃድ የተሰጣቸው መድሃኒት አምራቾች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እንደሚደረግ ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ 773 ናሙና ተወስዶ ፍተሻ ስለመደረጉ ለአብነት ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም