የ26ኛው የመላው ኦሮሚያ የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር በሸገር ሲቲ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

141

ጅማ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡-  በጅማ ከተማ ለ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የ26ኛው የመላው ኦሮሚያ የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር በሸገር ሲቲ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ።

በሻምፒዮና ውድድሩ የሸገር ሲቲ አስተዳደር 47 የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት 1ኛ ሲሆን አዳማ 45 እና ማያ ከተማ 23 የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

የእግርና የእጅ ኳስን ጨምሮ በ21 የስፖርት አይነቶች በተካሄደው ውድድሩ ከ5ሺህ በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።


 

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ማቴዎስ ሰቦቃ በስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት ስፖርት በማንኛውም ልዩነቶች ሳይገደብ  በእኩልነት እና በእውነተኛ ፍቅርና ወንድማማችነት የሚደረግ ውድድር ነው።

ዘርፉ የአገሪቱን ልማት በማፋጠንና ኢኮኖሚውን በማሳደግ ረገድ ያለውን ሚና አንስተው ልዩነቶችን በመፍታትና ዘላቂ ሰላምን በማስፈንም ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል።

“ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ለመዝናናት ተወዳጅና ተመራጭ ዘርፍ እየሆነ መጥቷል” ያሉት ሀላፊው “ዘርፉን በበለጠ ለማጎልበት እየሰራን ነው” ብለዋል።

 ይህንን የአንድነታችን፣ የእድገታችንና መሰረት የሆነውን ወሳኝ ዘርፍ በማጠናከር ለሀገር ልማት ለማዋል  በትኩረት እየተሰራ  ነው” ሲሉም አክለዋል።

26ኛው የመላው ኦሮሚያ ጨዋታ ስፖርት ውድድር የአንድነት እና አብሮ የመኖር መሰረት በተግባር ማሳየቱን አስታውቀዋል።

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው ጅማን ለዚህ ውድድር በመመረጧ ለከተማዋ ጥቅም ሚያስገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ስፖርት ወዳጅነትና መቀራረብን ፍቅርና ስላምን የሚያመላክት መሆኑን ገልጸው “የስፖርቱን ዘርፍ ለማጎልበት በትብብር መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል።

በ26ኛው የመላው አሮሚያ የስፖርት ሻምፒዮና የሽልማት እና የመዝጊያ መርሃግብር ላይ የስፖርቱ ዘርፍ የስራ ሀላፊዎች የስፖርቱ ቤተሰብና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም