በወገራ ወረዳ በእንቃሽ እና አካባቢው በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ

89

ባሕር ዳር፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ በእንቃሽ እና አካባቢው ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 ታጣቂዎች የሰላም አማራጩን ተቀብለው ወደ ሕዝብ እና መንግሥት ተመልሰዋል።

የሰላም አማራጩን ተቀብለው የተቀላቀሉ ታጣቂዎችም ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ መንግሥት ላደረገላቸው ይቅርታ አመሥግነው በቀጣይ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ተመልሰው የአካባቢያቸውን ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።


 

በወረዳው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝም የወገራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይናገር ወረታው ተናግረዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው ፀረ ሰላም እና ፀረ ልማት አጀንዳ በማራገብ ኅብረተሰቡን ለእኩይ ድርጊት የሚያነሳሱ ግለሰቦችን መታገል አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ለዚህ ደግሞ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ በመሥራት ለዘላቂ ሰላም መትጋት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የሚፈጠሩ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት መሞከር ተገቢ መሆኑን ኀላፊው አንስተዋል፡፡

ሰላምን ማረጋገጥ የሁሉም ድርሻ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባው ዋና አሥተዳዳሪው መናገራቸውን የዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም