ለመጪው የትንሣኤ በዓል መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል - የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን

146

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- ለመጪው የትንሣኤ በዓል መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚገመት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሸማች ማኅበራት በኩል እንደሚያቀርብ ነው የገለጸው።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሀብተየስ ዲሮ እንደገለጹት ለትንሣኤ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ሥራ ጀምሯል።

በዚህም ጤፍ፣ ዱቄት፣ የቁም እንስሳት፣ እንቁላል፣ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶች በዩኒየኖች አማካኝነት ወደ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል። 

ምርቶቹ በ800 የሸማቾች ሱቆችና በ137 የእሁድ ገበያዎች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

በሸማቾች ማህበራት ስር የሚገኙ 246 ስጋ ቤቶችም በኪሎ ከ400 እስከ 460 ብር እና በቅርጫ ሥጋን ለማቅረብም  ዝግጅት ማድርጋቸውን ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት።


 

በኮሚሽኑ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ተጫነ አዱኛ በበኩላቸው፥ ለበዓሉ የሚቀርቡ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በትክክል እንዲደርሱ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም