የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የቆላማ ስርአተ ምህዳር የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ፕሮጀክት እየተገበረ ነው

223

መቀሌ ፤ሚያዚያ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች 120 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቆላማ ስርአተ ምህዳር የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ፕሮጀክት እየተገበረ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። 

ፕሮጀክቱን በትግራይ ክልል ለማስጀመር በተዘጋጀ የትውውቅ መድረክ ላይ እንደተመለከተው፣ ፕሮጀክቱ በቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች 120 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።  

በባለስልጣኑ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ሙሉጌታ እንደገለጹት የቆላማ ስርአተ ምህዳር የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ፕሮጀክት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እየተተገበረ ይገኛል።

በፕሮጀክቱም በዋነኛነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ያለው የአካባቢ ስነምህዳር እንዲያገግም ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

በተለይ በቆላማ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የአፈር መከላትን ለመከላከል የደን ልማት ጥበቃ ሥራን ጨምሮ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ የሥራ እድሎች እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል። 

ከእዚህ በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ መሻሻል የበኩላቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ደሳለኝ ያስረዱት።

በዚህም ነዋሪዎች የአየር ንብረትን በማይጎዱ የልማት ሥራዎች እንዲሰማሩና እንደ ሶላር ያሉ የሃይል አማራጮችን የመጠቀም ባህላቸው እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ካለፋት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ፕሮጀክቱን እየተገበረ ይገኛል ያሉት አስተባባሪው፣ ፕሮጀክቱ በትግራይ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተገበር ቢቆይም አሁን ወደስራ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን በሁለት የትግራይ ወረዳዎች በሚገኙ አራት የገጠር ቀበሌዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስጀመር መታቀዱንና የዛሬው መድረክም ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። 


 

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ባለስልጣን ሀላፊ አቶ ፀጋይ ገብረማሪያም በበኩላቸው እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ በትግራይ ዘግይቶ ቢጀመረም በህዝቡ የተደራጀ ተሳትፎ ለማሳካት ጠንክረን እንሰራልን በለዋል።

ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ከሁለቱ ወረዳዎች እና ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ፕሮጀክቱን በተፋጠነ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም