በስታርትአፕ ዐውደ ርዕይ የቀረቡ የፈጠራ ሀሳቦችና ቴክኖሎጂዎች ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ ሰጭ ናቸው

147

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- በስታርትአፕ ዐውደ ርዕይ የቀረቡ የፈጠራ ሀሳቦችና ቴክኖሎጂዎች ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ ሰጭ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽመልስ እሸቱ ገለጹ።

ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው የስታርትአፕ ኢትዮጵያ ዐውደ ርዕይ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የተቋማት ኃላፊዎች እየተጎበኘ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዐውደ ርዕዩ ጎብኝዎች እንዳሉት በስታርትአፖች የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል ብሩህ የሚያደርጉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ በዐውደ ርዕዩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዕድገት እንዲመዘገብ የሚያስችሉ ፈጠራዎችን መመልከታቸውን።

የስታርትአፕ የፈጠራ ስራዎች በአግባቡ ከታገዙ የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ተስፋ ሰጭ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ኮርፖሬሽኑ ቴክኖሎጂዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ የራሱን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

ሀገራዊ ልማቱ ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች መደገፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዐውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎችም የተቋማትን ምርትና አገልግሎት የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት አቶ ተስፋ አበባና በአዲስ አበባ የልደታ ማኑፋከቸሪንግ ኮሌጅ ተማሪዋ ማህሌት ገብሬ እንዳሉት የስታርትአፕ ቴክኖሎጂዎች ሀገርን ወደ ተሻለ ልማት ያሸጋግራሉ።

ስታርትአፕን መደገፍ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ካለው ቁልፍ ፋይዳ አኳያ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህም የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች ይበልጥ ማበረታታት ይገባል ነው ያሉት።

ለዕይታ የቀረቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የነገዋ ኢትዮጵያን ለማዘመን ብሩህ ተሰፋ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የስታርትአፕ ዐውደ ርዕዩ እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ይቀጥላል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ 500 የሚጠጉ ስታርትአፖች እየተሳተፉ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም