ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር ይጀምራል 

146

ሀዋሳ፣ሚያዚያ 17/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች መረጣ ባካሄደባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር እንደሚጀምር የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስታወቁ።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሂደት መሠረታዊና የህዝብ ተሳትፎ ባማከለ መልኩ የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ በ10 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች አገባዷል።

በነዚህ አካባቢዎች ያገኛቸውን ልምድ በመጠቀም በአማራና በትግራይ ክልሎች የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታና መረጣ ቀሪ ስራዎች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል። 

በአሁኑ ወቅት የተሳታፊዎች መረጣ ባካሄደባቸው ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ውሰጥ ሰሞኑን አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

"ለዚህም በየወረዳው የተመረጡ ተወካዮች ወደ ክልላቸው ይመጡና በክልሉ ከሚገኙ 20 ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የክልላቸውን፣የአካባቢያቸውን ሀገራዊ የሚባሉ አጀንዳዎች ይሰጣሉ "ብለዋል።


 

ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብና መምህራንን ጨምሮ የሁሉም ህብረተሰብ ተወካዮች ለየብቻቸው ከተወያዩ በኋላ በጋራ ያመጡትን አጀንዳ አደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚልኩ አስረድተዋል።

"እነዚህ የተላኩ አጀንዳዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ታዛቢዎች ባሉበት ግልፅ በሆነ መስፈርት ከተመረጡ በኋላ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አጀንዳዎች ከተለዩ በኋላ ሀገራዊ ምክክር ይካሄዳል" ብለዋል።

ይህንን ለማድረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቀረው ጊዜ 10 ወር መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አስታውቀዋል።

"በነዚህ ጊዜያት ውስጥ የጎላ እንቅፋት እስካላጋጠመው ድረስ ቢያንስ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔውን አስጀምሮና የተወሰኑ አጀንዳዎችን ወደ ማግባባት በማምጣት ማጠናቀቅ እንደሚችል ሙሉ እምነት አለን" ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል። 

"ኮሚሽኑ የህዝብ ወገንተኛ መሆኑን በስራችን ለማሳየት እየተጋን እንገኛለን" ሲሉም ተናግረዋል።

የሀገራችን ህዝቦች ለብዙ ሺህ ዘመናት ተዋደው፣ተጋብተው፣ተጋምደውና ተስማምተው የኖሩ በመሆናቸው በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ መድረስ እንደማያዳግታቸው ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል።  

በሀገራዊ ምክክሩ የኦሮሚያ ክልል የተሳታፊዎች መረጣና ልየታ ማጠቃለያ መርሀ ግብር በሻሸመኔ ከተማ መካሄዱን  ይታወሳል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም