በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ታዳጊዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው -  ኢንስቲትዩቱ

195

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ታዳጊዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በመጪው ክረምት የስልጠና መርሐ ግብር የሚሳተፉ ተማሪዎችን ምዝገባ ጀምሯል።

በ3ኛ ዙር ስልጠና የሚሳተፉት የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑ እና በሳምንት ለ4 ቀናት መከታተል የሚችሉ መሆን እንደሚኖርባቸው ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ዕድገት መለኪያ የሆነ ዘርፍ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም ግንባር ቀደም አህጉራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተቋም በመገንባት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመስኩ የፈጠራ ዝንባሌ እና ክህሎት ላላቸው ታዳጊዎች የሚሰጠው ስልጠናም በዘርፈ ብዙ መስኮች ተወዳዳሪ ሀገር መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በመጪው ክረምት ታዳጊ ተማሪዎችን በመቀበል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ክህሎታቸውን በማበልጸግ የተሻለ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ስልጠናውም የኢትዮጵያን ከፍታ በማስቀጠል ፈጠራና ክህሎትን በማበረታታት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ታዳጊዎችን ማፍራት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የምርምርና ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር)፥ በክረምት ወራት የሚሰጠው ስልጠና እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም በኢንስቲትዩቱ ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ በክልሎች ለማስፋት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የቴክኖሎጂ አማካሪው ሰለሞን ሙሉጌታ፥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የሚሰጥ ስልጠና ታዳጊዎች የዓለምን አዝማሚያና ዝንባሌ በቅጡ እንዲረዱ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዕውቀትንም ለግብርና፣ ለመንግስት አገልግሎት፣ ለጤና እና ሌሎች ተግባራት እንዲያውሉት ማስተማር እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

በመጪው ክረምት ለሁለት ተከታታይ ወራት በሚሰጠው ስልጠና ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎች ከሚያዝያ 17 እስከ ግንቦት 07/2016 ባሉት ቀናት መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል። 

ከሀምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 1/2016 ዓ.ም በሚቆየው ስልጠና ተማሪዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀትና ክህሎት የሚያገኙበት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርት ይሰጣቸዋል።

ስልጠናው ከሚያተኩርባቸው መካከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሰረታውያን፣ ሮቦቲክስ፣ ፕሮግራሚንግ፣ ማሽን ለርኒንግ እና ሌሎችም ይገኙበታል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም