ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ18 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ተከናውኗል

80

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡-ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ18 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማከናወን መቻሉን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቋሙን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጡ ከ24 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራዎቹ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ደም ልገሳ፣ የመንገድ ደኅንነት አገልግሎት፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ጨምሮ በ13 የስምሪት መስኮች የተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።

በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ወጣቶቹ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውረው አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የበጎ ፈቃደኝነት ግንዛቤና አስተሳሰብን ማዳበራቸውንና የሕዝቡን ማኅበራዊ ትስስር ማሳደጋቸውን ገልፀዋል።

አገልግሎቱ ወጣቶች የሌሎችን ባህል፣ እሴትና ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ወጣቶቹ በሰጡት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ18 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎቶች መከናወናቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።

በወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ58 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ940 ሺህ በላይ ወጣቶችን በሰላም ግንባታና ግጭት መከላከል ሥራ ላይ ማሳተፉም ተገልጿል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም