ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከመንግስት ባለፈ የሁሉም ዜጎችና ተቋማት ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት 

94

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከመንግስት ባለፈ የሁሉም ዜጎችና ተቋማት ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የጸረ ሙስና ስምምነቶችን በመቀበል እና ሀገራዊ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ለተግባራዊነቱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

በተለይም ከለውጡ በኋላ የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1236/2013 እንደገና እንዲቋቋም ተደርጓል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ሀገር ስር የሰደደውን ሌብነት ለመከላከል ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረጋቸው ይታወቃል።

የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን በመቀበል እንደ ሀገር ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የህዝብና መንግስት ሀብት ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ በሪፖርቱ አረጋግጧል።

በፌደራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስቸኳይ የሙስና መከላከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ጋሻው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ የሥነ ምግባር አቅም ግንባታ፣ የሙስና ቅድመ መከላከል እና ህግ ማስከበር ስራዎችን እያከናወነ ነው።

ከፌዴራል፣ ከክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ጋር በመቀናጀት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራትና የትምህርት ተቋማትን አስተባብሮ የሥነ ምግባር ትምህርት በመስጠት የህብረተሰቡን ሙስናና ብልሹ አሰራር የማጋለጥ ባህል ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ጥናት በማካሄድና የሃብት ምዝገባ በማከናወን ሙስናን ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በዲጂታል እና በተለያዩ አማራጮች 65 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን በመቀበል ለፍትህ አካላት ቀርቦ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እንደ ሀገር 373 የሙስና ቅድመ መከላከል ሥራዎች በማከናወን ከአንድ ነጥብ 384 ቢሊዬን ብር በላይ የህዝብና መንግስት ሃብት እንዲሁም ከ25 ሚሊዬን ካሬ ሜትር በላይ የሆነ የከተማ እና ገጠር መሬት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን አስታወሰዋል።

በ25 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋማት የሙስና ስጋት ያለባቸው ዘርፎችን አሰራር በማጥናት በውጤቱ መሰረት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሀብት ምዝገባ፣ በእድሳትና አገልግሎት በማቋረጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት እስካሁን የዘጠኝ ሺህ 992 የፌደራል የሥራ ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች ሀብት ምዝገባ ማከናወኑን ተናግረዋል።

መንግስት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ጉዳዩ  የሁሉንም ግለሰቦችና ተቋማት ርብርብ የሚፈልግ መሆኑን ነው የገለጹት። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም