ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የሚተገበር ውጤታማ የጤና አመራር መርሐ ግብርን ይፋ አደረገች

56

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የጤና ሚኒስቴር ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የሚተገበር ሀገር አቀፍ ውጤታማ የጤና አመራር መርሐ ግብርን ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፤ በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ቢሆንም የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ውጤታማ የጤና አመራር መገንባት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለዚህም ውጤታማ የጤና አመራር መርሐ ግብር(ፕሮግራም) ትግበራ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት በስራ ላይ ይውላል ነው ያሉት።

የመርሐ ግብሩ ዓላማም ለጤናው መስክ ብቁ አመራርን መፍጠር፣ የሴቶችን እና የዘርፉ ተተኪ ወጣት አመራሮችን ተሳትፎና አቅም ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ያለውን ውስን ሀብት በመጠቀም የጤና ዘርፉን ለማሳደግ ውጤታማ አመራር መገንባት የግድ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎም ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ባለፉት ጊዜያት የህክምና ስርዓቱ እየተሻሻለ ቢመጣም ሙያዊ ክፍፍሎች በመኖራቸው የቡድን ስራ እየቀነሰ መምጣቱ ተግዳሮት ፈጥሯል ነው ያሉት።

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ በስድስት ዓመቱ መርሐ ግብር በሙያው የሰለጠኑ እና የጤናውን ዘርፍ በጥራትና በብቃት የሚመሩ አመራሮችን (Clinical Leaders) ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።

አመራርነትን ከተጠያቂነት ጋር በማያያዝ ውጤታማ የጤና አገልግሎትን ለማስፋት ትኩረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ውጤታማ የጤና አመራር መርሐ ግብር ትግበራ በተያዘው ዓመት የተጀመረ ሲሆን እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ እንደሚቆይም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም