በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር  እስካሁን 500 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ ተዘጋጅቷል 

131

 አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር  እስካሁን 500 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ መዘጋጀቱን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል  አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩም ተገልጿል።

የቢሮው የደን ልማትና እንክብካቤ ዳይሬክተር ከተማ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራን ከተፋሰስ ልማትና ከሌማት  ትሩፋት መርሐ ግብር ጋር  በማቀናጀት  እየተሰራ ነው። 

በክልሉ ባለፉት ዓመታት 18 ነጥብ 6 ቢሊዮን  ችግኝ መተከሉን አስታውሰው የፅድቀት  መጠን  በአማካኝ ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ በመጪው ክረምት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዶ እስካሁን 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ ዝግጁ ማድረጉን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 500 ሚሊዮኑ ለፍራፍሬ ምግብነት የሚውሉ ናቸው ብለዋል።

ለደንና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችም ዝግጁ  የማድረግ ስራዎች  እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

 በአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ለዜጎች የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በቋሚነት ከ80 ሺህ በላይ ሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ  መቻሉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።  

የአረንጓዴ አሻራን ከተፋሰስ ልማትና ከሌማት ትሩፋት ጋር በማቀናጀት ዜጎች ችግኞችን በመንከባከብ ፍራፍሬ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ  እየሆኑ ነው ብለዋል።

ወጣት ዲቢሳ ጋሹ እና ጥላሁን ደርሶ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በማህበር በመደራጀት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር  የስራ እድል እንደተፈጠረላቸውና በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በችግኝ ማፍላትና ሌሎችም ስራዎች በትጋት በመስራት ገቢያቸው እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዳላቸው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም