ሰላምና ልማትን የማጠናከር ስራ በትኩረት ይከናወናል  -ከንቲባ ከድር ጁሃር

109

ድሬዳዋ ፤ ሚያዝያ 17/2016 (ኢዜአ)፡- የሰላምና የልማት ውጤታማ ተግባራትን የማጠናከር ስራ በትኩረት ይከናወናል ሲሉ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።

ለድሬዳዋ አስተዳደር የፖሊስ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት  አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ ለውጥና አደረጃጀት የተገነባው ፖሊስ በአርአያነት የሚጠቀሱ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ህዝባዊነቱን አፅንቶ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ባከናወናቸው ተግባራት በድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ መኖሩን ጠቅሰዋል።

ሰላምና ፀጥታው  በገጠርና በከተማ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል  ሲሉም አክለዋል።

ስራዎቹን ይበልጥ ለማሳደግ የፖሊስ አመራሮችን አቅም የመገንባት ስራም በትኩረት ይተገበራል ብለዋል።


 

የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው ፖሊስ በዘመናዊ አሠራርና በቴክኖሎጂ ተደግፎ የነዋሪዎችን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል።

“ለውጡን ተከትሎ ባከናወናቸው ተግባራት የተገኙ ፍሬዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በተሞክሮነት ተቀምረው እየተስፋፉ ናቸው” ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነር አለሙ ገለፃ  ስራዎቹን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚሰጠው ስልጠና በቁርጠኝነት ይተገበራል።

ለሁለት ቀናት በሚሰጠው የሙያ ስነምግባርና የመረጃ መር አገልገሎት የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ የአስተዳደሩ የፖሊስ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም