በቴክኖሎጂ የታገዘ የቡና ልማት በማከናወን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኘን ነው 

124

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የቡና ልማት ፓኬጅን በመተግበርና በቴክኖሎጂ የታገዘ ልማት በማከናወን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኘን ነው ሲሉ በሲዳማ ክልል የሸበዲኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ። 

የክልሉ ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን በበኩሉ ቡና አብቃይ በሆኑ ወረዳዎች 74 የቡና ቴክኖሎጂ መንደሮችን በመፍጠር ከ65 ሄክታር በላይ ማሳ በቡና እየለማ መሆኑን አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮቹ እንደገለጹት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን፣ ፓኬጆችንና የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በክላስተር ካለሙት ቡና ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኙ ነው።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ዮሴፍ ተፈሪ እንዳሉት አራት ሄክታር በሚጠጋ መሬታቸው ላይ የተሻሻለ የቡና ዝርያን ጨምሮ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቡና እያለሙ ነው።

ባለፈው ዓመት 160 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰው በቴክኖሎጂ ታግዘው ቡና ማልማት መጀመራቸው የተሻለ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮ ተከላ 2ሺህ 600 የቡና ችግኝ ለመትከል ዝግጅት አጠናቀው ወደ ተግባር መግባታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ በልማቱ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደሚጠቀሙና የቡና ፓኬጆችን እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።    


 

ሌላኛው አርሶ አደር ካሳ ተኮን በበኩላቸው በ3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ቡና እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ዝርያቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ተክለው በክላስተር በማልማታቸው በየዓመቱ የሚያገኙት ምርት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የቡና ልማት ሥራን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑን የጠቀሱት አርሶ አደሩ፣ "በሁለት ዓመት ከሰበሰብኩት ቡና እስከ 80 ሺህ ብር አግኝቻለሁ" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የቡና ተከላ ሥራቸውን በልምድ እንደሚያከናውኑ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት የጉድጓድ ዝግጅትና የተሻሻለ ዝርያን ጨምሮ ሙሉ የቡና ልማት ፓኬጅን መተግበራቸውን ገልጸዋል።


 

የሸበዲኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ አየለ በበኩላቸው በወረዳው በ10ሺህ 250 ሄክታር መሬት ላይ ቡና እየለማ መሆኑንና ምርቱም በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ኤሊያስ ገለጻ ዘንድሮ በ527 ሄክታር መሬት ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው አዲስ የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።

የማሳ ሽፋኑን ለማሳደግ በተቀመጠ አቅጣጫ ባህር ዛፍ ያለባቸውን መሬቶች በቡና እና በፍራፍሬ ተክሎች ለመተካት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በክልሉ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ለቡና ፓኬጆች አተገባበር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሻሻለ የቡና ዝርያ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያና የጥላ ዛፍ ተከላን ጨምሮ ለምርታማነት አስተዋጾ ያለው የቡና ልማት ፓኬጅ አጠቃቀምን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ከሄክታር የሚገኘውን 9 ነጥብ 5 ኩንታል ቡና ወደ 11 ነጥብ 5 ለማሳደግ ግብ መጣሉን ነው አቶ መስፍን ያመለከቱት።

 የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የቡና ቴክኖሎጂ መንደሮችን የመፍጠር ሥራ ማጠናከር አንዱ ነው። 

በዚህም በአስር ወረዳዎች ውስጥ 74 የቡና ቴክኖሎጂ መንደሮችን በመፍጠር በ65 ሄክታር መሬት ላይ አርሶ አደሩ የቡና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እንዲያለማና እንዲያሰፋ እየተደረገ ነው።

በቀጣይም ቡናን ስፔሻላይዝ በሚያደርጉ ወረዳዎች ተጨማሪ የቴክኖሎጂ መንደሮችን ለማስፋት እቅድ መያዙን አቶ መስፍን ተናግረዋል።።

በሲዳማ ክልል ከ165 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና እየለማ ሲሆን ለተያዘው ዓመትም ከ28 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም