በአዳማ እና ቢሾፍቱ የተጀመረውን የስማርት ከተማ ግንባታ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ማስፋፋት ይገባል- የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን 

118

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በአዳማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የተጀመረውን የስማርት ከተማ ግንባታ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ማስፋፋት እንዳለበት የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የስማርት ከተማ ግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በአዳማ ከተማ እና በቢሾፍቱ ከተማ በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በዚሁ ወቅት፥ መንግስት በ10 ዓመትና በመካከለኛ ዘመን ዕቅዱ ለስማርት ከተማ ግንባታ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

የስማርት ከተማ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ለክልሎች እና ከተሞች ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስልጠና በመስጠት በ2015 ዓ.ም አዳማ ከተማን እንደ ሞዴል በመውሰድ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

ከስማርት ከተማ ግንባታ ምሰሶዎች ውስጥ ለ”ስማርት አስተዳደር” ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ክልሎችም ከተሞቻቸውን ስማርት ለማድረግ ተነሳሽነት እያሳዩ እንደሆነ ገልጸው በጅማ፣ ባህር ዳር፣  ደብረ ብርሃን፣  ደሴ፣  ሆሳዕና፣  ቡታጂራ፣  አርባምንጭ እና ወላይታ ሶዶ ጅምር ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።


 

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በከተማዋ የተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል። 

አገልግሎትን ከማቀላጠፍ ባሻገር የመንግስትን የማስፈፀም አቅም እንዲጎለብትና ብልሹ አሰራሮች እንዲቀንሱ አድርጓል ነው ያሉት። 


 

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታል ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። 

የከተማ መሬት ይዞታን ወደ ካዳስተር በማስገባት የይዞታ ማረጋገጫ በኦንላይን መከናወኑን አንስተው፥ ይህም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን እንደሚያቀላጥፍ ጠቅሰዋል። 


 

የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን መሪ አቶ ተገኔ ኃይሉ በአዳማና በቢሾፍቱ ከተሞች ያለው የቴክኖሎጂና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በከተሞቹ የመሬት ይዞታዎችን ወደ ካዳስተር የማስገባት እና የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባን በኦን ላይን  መፈጸሙ የስማርት ከተማ ግንባታን የሚያግዝ እንደሆነ አንስተዋል።

የከተማ አገልግሎቶችን በዲጂታል መስጠት መጀመራቸውም ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው እንደሆነ ገልጸዋል።

በአዳማና ቢሾፍቱ ወንጀልን ለመከላከል እና የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር  የ"ስማርት ሴኪዩሪቲ" ቴክኖሎጂ ከተቋማት ጀምሮ በዋና ዋና ጎዳናዎች መተግበሩ የሚበረታታ ነው ብለዋል።


 

የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባል አቶ አሸናፊ አበበ በበኩላቸው፥ ባለሙያዎችን በማብቃትና የዲጅታል መሰረተ ልማቶችን በማልማት አገልግሎቶችን ለማሳለጥ የጀመሩት ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በሁለቱ ከተሞች ያለውን ውጤታማ ተሞክሮ በሌሎች ከተሞች ማስፋፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም