ኢትዮጵያ ከኢንተርፖል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት አላት

77

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከኢንተርፖል ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳለት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ብሄራዊ ኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ ፖሊስ ትብብር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ ገለጹ።

ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ በኢንተርፖል ዋና ጽህፈት ቤት መቀመጫ ፈረንሳይ ሊዮን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 19ኛው የብሄራዊ ኢንተርፖል ቢሮ ኃላፊዎች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው።

የኢንተርፖል 19ኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ "የብሔራዊ ኢንተርፖል ቢሮዎችን ግንኙነት በማጠናከር የዓለም ወንጀል ስጋቶችን መቀነስ" በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያዚያ 15-17 ቀን 2016 ዓ.ም እየተካሄደ ይገኛል።

ረዳት ኮሚሽነሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኢንተርፖል አገልግሎት ማስፋፋት ፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከተቋሙ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ያላትን ፍላጎት ገልጸዋል።

በተለይ የፎረንሲክ እና የሳይበር ወንጀል ምርመራን አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እያካሄደ ባለው ሪፎረም፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እንዲሁም በድርጅቱ ዳታ ቤዝ አጠቃቀም ላይ ከኢንተርፖል ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት መኖሩን አብራርተዋል።


 

የኢንተርፖል አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ፖሊስ የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የማቴሪያል ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በጉባኤው ላይ የሀገራት የብሔራዊ ኢንተርፖል ቢሮ ኃላፊዎች እና ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ መሆኑን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የየሀገራቱ ኢንተርፖል ቢሮዎች ባለፈው ዓመት ስላከናወኗቸው እና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም የሀገራት ምርጥ ተመክሮዎች እየቀረቡ ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን ከውይይቱ በኋላ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል፡፡

ኢንተርፖል ከተመሠረተ አንድ መቶ ዓመት ያለፈው ሲሆን 196 አባል ሀገራትን ያቀፈና ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. ከ1958 ጀምሮ የድርጅቱ አባል ሀገር መሆኗ በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም