የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነው ሸበሌይ ሪዞርት ግንባታ የክልሉ የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳደግ ተገለጸ

91

ጅግጅጋ ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የገበታ ለትውልድ   ፕሮጀክት አካል  የሆነው የሸበሌይ ሪዞርት ግንባታ ሲጠናቀቅ የሶማሌ ክልልን  ቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግ የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ኡመር  ገለጹ።

የሸበሌይ ሪዞርት የግንባታ ሂደት  የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር  ዶክተር አብረሃም በላይ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ፣የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ኡመር እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጎብኝተዋል። 


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በወቅቱ እንዳሉት ፤ የሸበሌ ሪዞርት በክልሉ የመጀመሪያ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆን ነው።

"ግንባታው ሲጠናቀቅ በአካባቢው የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል "ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የሀገር ሀብት እንደሚገነባ አመልክተው፤ የአካባቢው ህብረተሰብ በስፍራው ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የሸበሌይ ሪዞርት ፕሮጀክት  በስምንት መንደሮች የተከፋፈሉ የመዝናኛ ሥፍራዎችና የመሰብሰቢያ አደራሾች ከሚያካትታቸው መገልገያዎች እንደሚገኙበት  የገለጹት ደግሞ  የሸበሌይ ሪዞርት ስራ አስከያጅ ኢንጅነር አህመድ ሹክሪ ናቸው። 

እንዲሁም የልጆች መዝናኛ፣ አስራ አራት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡ ግንባታዎችም አካተዋል  ብለዋል። 

ግንባታው አሁን ላይ 33 በመቶ መድረሱን ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ፤ የመጀመሪያ ዙር ግንባታውን በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። 


 

የሸበሌይ ሪዞርት የውሃ አቅርቦት ዙሪያ በሶማሌ ክልል የዲዛይን እና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ባለሙያዎች የተሰራውን ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል። 

ከጉብኝቱ በኋላ የስራ ሃላፊዎቹ በፕሮጀክቱ አካባቢ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

ከጅግጅጋ   ከተማ 29 ኪሎ ሜትር ርቀት 385 ሄክታር በሚሸፍን ስፍራ ላይ የሚገነባው ፕሮጀክቱ የጅግጅጋ   ከተማ እና የአካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻነት የሚለውጠው የቱሪዝም ስራ አንድ አካል እንደሆነ ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም