የብሪክስ ጥምረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ሚና ለማጠናከር ዕድል የሚፈጥር ነው

89

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የብሪክስ ጥምረት በአባል ሀገራቱ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ሚና በልምድ ልውውጥና በፋይናንስ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን  ገለጸ።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሩሲያ ከመጡ የብሪክስ ጥምረት  የሲቪል ማህበረሰብ  ባለሙያዎችና ከተለያዩ  የሲቪል ማህበራት ጋር  ውይይት እያደረገ ነው። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በዚሁ ወቅት፥ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት  ሰፊ ሪፎርም  ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የህግ ማሻሻያ በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በሁለንተናዊ ሀገራዊ ልማት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ  ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሩሲያ እና ከሌሎች አባል ሀገራት በሚኖራት ትስስር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰፊ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም እንዲኖራቸው ዕድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

የብሪክስ ጥምረት 10 ሀገራት ያሉት ሲሆን የዓለምን 37 በመቶ ኢኮኖሚ  እንዲሁም 45 በመቶ የዓለም ህዝብ ቁጥርን ያቀፈ ግዙፍ የትብብር ማዕቀፍ መሆኑ ይታወቃል።

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ እና ደቡብ አፍሪካ የብሪክስ መስራቾች ሲሆኑ፥ ኢትዮጵያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ግብፅ እና ኢራን በዚህ ዓመት ጥምረቱን ተቀላቅለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም