በክልሉ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት ይሰራል--- አቶ ኦርዲን በድሪ

82

ሐረር ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች በጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት ይሰራል ሲሉ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ  ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩና የካቢኔ አባላት በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በካፒታል ፕሮጀክት የተከናወኑ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው እየጎበኙ ነው።


 

እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል ተቋማት የሚያከናውኗቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያሉበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች የሚመልሱ የመንገድ፣ የውሃ፣ የትምህርት፣ የመስኖ፣ የኤሌትሪክና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች በዋናነት የተጎበኙ የልማት ፕሮጀክቶች ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ  ጉብኝቱ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን በጊዜ፣ በጥራት፣ በቁርጠኝነት ከመስራት እና የተመደበውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋሉ ከማረጋገጥ ባለፈ የገጠሙ ውስን ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመፍታት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በተለይ በከተማው የሚገኘው የምስራቅ እዝ መከላከያ ሠራዊት እያከናወናቸው ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እዙ ባዶ ቦታዎችን ወደ ልማት ለማስገባት በራስ አቅም እያከናወነ የሚገኘው ስራ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን የሚያከናውነው የልማት ስራ ተሞክሮ የሚወሰድበት እና በእዙና ክልሉ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ያሉት አቶ ኦርዲን፣ ለፕሮጀክቶቹ ውጤታማነት የክልሉ መንግስትም እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሠራዊቱ የሀገርን ልዑዓላዊነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በልማት ስራዎች እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሃመድ ተሰማ ናቸው።

ለእዚህም እዙ በምስራቅ ሐረርጌ ባቢሌ ወረዳ ኤረር ቀበሌ ገበሬ ማህበር የእርሻ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በከተማው በሚገኙ ሁለት ቦታዎች ላይ እዙ የግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ የክልሉ መንግስት ከሰራዊቱ ጎን በመሆን ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የመስክ ምልከታ ላይ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሴክተር መስሪያ ቤት ሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም