ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከበቂ በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ተመልከተናል - የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን

114

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከበቂ በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን በመስክ ምልከታ ማረጋገጡን የፌደራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ።

ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ መጪው ክረምት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን በዝግጅት ደረጃ ከእቅድ በላይ 7 ቢሊዮን ችግኝ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የግብርና ሚኒስቴርን የመጪው ክረምት የአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዝግጅትና በባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞችንና የተፋሰስ ልማት ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ተመልክቷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኑሴ መኮንን፥ ኢትዮጵያ  በአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዜጎችን በማሳተፍ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በአማካይ ከ87 በመቶ በላይ መፅደቃቸውን ተናግረዋል።

በመጪው ክረምት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን በዝግጅት ደረጃ ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነትና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ሲሆን 40 በመቶ  ደግሞ ለደን ችግኝ የሚተከሉ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የስፔስ ሳይንስና የጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የሱፐርቪዥን ቡድኑ መሪ አቶ አብዲሳ ይልማ፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅኖን መቋቋምና የምግብ ዋስትናን መረጋገጥ እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።


 

መርሐ ግብሩን ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ጋር በማቀናጀት መተግበሩ የተራቆቱ አካባቢዎችና የደረቁ ምንጮች እንዲያገግሙ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያስቻለ ነው ብለዋል።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቂ ችግኝ የመትከያ ቦታ መዘጋጀቱን እንደተመለከተ ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ችግኞችን በዝግጅት ወቅትና ከተተከሉ በኋላ ያሉበትን ደረጃ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር መከታተልና መንከባከብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም