የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ለበርካታ ዓመታት ያልሰበሰበውን ውዝፍ ሂሳብ በፍጥነት ሊሰበስብ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

95

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ለበርካታ ዓመታት ያልሰበሰበውን ውዝፍ ሂሳብ በፍጥነት እንዲሰበስብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን  የ2014/15 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ውይይት አድርጓል።


 

ግኝቱ የኮርፖሬሽኑን ምርጥ ዘር፣ አግሮ ኬሚካሎችና የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት፣ ስርጭት፣ የብድር አመላለስ፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ነው።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ኮርፖሬሽኑ ከ10 ዓመት በላይ የቆየ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ሂሳብ አለመሰብሰቡንና ወደ መንግስት ካዝና አለማስገባቱን ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ የቆዩ ብድሮች እንዲመለሱ አለማድረጉን አንስተዋል።

የኮርፖሬሽኑ የግብርና ኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒትና የእርሻ ማሽነሪዎች አቅርቦት፣ የምርጥ ዘር አቅርቦትና የሜካናይዜሽን ማስፋፊያ አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በያዛቸው ቦታዎች ላይ የሚፈለገውን የልማት ስራ እያከናወነ ባለመሆኑ ምክንያት በክልሎች የወሰዳቸውን መሬቶች እስከ መቀማት መድረሱን ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የተገዙ ማሽነሪዎችን ከመጋዘን ውጪ ለብልሽት በሚዳርግ ሁኔታ ማስቀመጡን ግኝቱ እንደሚያሳይ አመልክተዋል።  

ከንብረት አጠቃቀም ጋር በተያያዘም ግምታቸው ከ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎችና በኬሚካል የተነከሩ የእህል ዘሮች ሳይወገዱ መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ግኝቶቹን በማረምና በማስተካከል ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ኮርፖሬሽኑ የፌደራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ፈጣን ማስተካከያና እርምት እንዲወስድ አሳስበዋል።

በተለይም ለበርካታ ዓመታት ያልሰበሰበውን ውዝፍ ሂሳብ በአስቸኳይ መሰብሰብ እንዳለበት አመልክተዋል።

 በተለይ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ኬሚካሎችና በኬሚካል ተነክሮ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ምርጥ ዘር  በአግባቡ ማስወገድ እንዳለበት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን የተጣለበትን ኃላፊነት በውል በመረዳት ለአርሶ አደሮች የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በሚፈለገው ጊዜ ማቅረብ እንዳለበት ነው ሰብሳቢዋ የገለጹት።

ኮርፖሬሽኑ ለማልማት የወሰደውን መሬት በአግባቡ መጠቀምና ማሽነሪዎችና ንብረቶችን ብልሽት እንዳይደርስባቸው በሼዶችና በመጋዘኖች በተገቢው ሁኔታ ማስቀመጥና  ወደ ስራ ማስገባት እንዳለበት ተናግረዋል።

ተቋሙ ሕግና ስርዓትን ባከበረ መልኩ ግዢ ከመፈጸም አኳያ ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

ኮርፖሬሽኑ  የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መታረምና መስተካከል አለባቸው ብሎ የሰጠውን አስተያየት በመውሰድ የተስተካከለ ሪፖርት እስከ ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ እንዲያቀርብ ሰብሳቢዋ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡  


 

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በኦዲት ሪፖርቱ የተጠቀሱ ግኝቶች ለማስተካከል የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከውዝፍ ሂሳብ ጋር በተያያዘ የተወሰነውን መሰብሰብ መጀመሩንና ለረጅም ጊዜ የቆዩ ብድሮችን ለዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በማሳወቅ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ተቋሙ ለረጅም ጊዜ የቆዩት ኬሚካሎቹ እንዲወገዱ ለመንግስት ንብረት አስወጋጅ ኮሚቴና ለግብርና ሚኒስቴር ማሳወቁንና ምላሻቸውን እየጠበቀ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከግብዓት አቅርቦት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት ከነባር አቅራቢዎች በተጨማሪ ከሌሎች ክልሎች ጋር በመነጋገር ግብአቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት። 

በሌላ በኩል ጊዜያቸው ያለፈባቸውን የእርሻ መሳሪያዎችና ማሽነሪዎችን በማስወገድ በአዲስ አቅርቦት ለመተካት የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል። 

በክልሎች ያሉትን መሬቶች በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል ከሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።

ኮርፖሬሽኑ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም