የኦሮሚያ ክልል ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

105

ቦረና፤ ሚያዝያ  17/2016(ኢዜአ)፡- የኦሮሚያ ክልል ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ።

የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በቦረና ዞን ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ የክልሉ መንግስት ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ከአጭር ጊዜ እቅድ መካከል ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በድርቅ ምክንያት ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ ተከታታይ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ስራም በክልሉ የተወሰኑ ቦታዎች በተከሰተ ድርቅ ምክንያት በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከረጅም ጊዜ ዕቅድ አንጻርም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያሳኩ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን አቶ ኃይሉ አስረድተዋል። 

እንደ እሳቸው ገለጻ በክልሉ እየተተገበሩ ከሚገኙ 73 ፕሮጀክቶች መካከል 36ቱ ድርቅ በሚያጠቃቸው ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ በዋናነት አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርሶ አደርነት የሚለውጡ የመስኖ መሰረተ ልማቶች፣ የመጠጥ ውሃ እና የመኖ ልማት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ ገልጸዋል።

የቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በሪሶ ገኖ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የ18 አነስተኛ ግድቦች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።


 

የአብዛኛዎቹ ግድቦች ግንባታ መጠናቀቁን የጠቆሙት አቶ በሪሶ፣ በተሰራው የበጋ መስኖ ልማት ስራም በሄክታር እስከ 75 ኩንታል በቆሎ መገኘቱንና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም መከናወኑን ገልጸዋል።

በእንስሳት መኖ ልማትም 75 ሺህ ቶን መኖ ተዘጋጅቶ መከማቸቱን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ከተሳተፉት የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች መካከል የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱራህማን ሩቤ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን የልማት ስራዎችን በተከታታይ መዘገብ አለባቸው ብለዋል።

ችግሮች ሲከሰቱ ብቻ ከመዘገብ የዜጎችን ህይወት ለመቀየር የሚከናወኑ ሥራዎችንም ለህዝቡ ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም