በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 75ቱ መጠናቀቃቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ

79

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 17/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል  በመገንባት ላይ  ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ  75 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  መጠናቀቃቸውን  የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ፤ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተለይ በመልሶ መቋቋም ጽህፈት ቤትና በክልሉ መንግስት በተመደበ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመገንባት ላይ ካሉ 50 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 42ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን አመልክተዋል።


 

እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ  እየተገነቡ ካሉ  45 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 33ቱ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። 

በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ያለውን ጥበት ችግር ለማቃለል የተገነቡ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እንዳሉም  ተጠቅሷል።


 

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የአስተዳደር፣ የቤተ ሙከራ፣ የቤተ መፃህፍትና የአይሲቲ ህንፃዎችና ክፍሎችን አካተው መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኙ ቀሪዎቹ 20 የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

ትምህርት ቤቶቹ በቀጣይ ዓመት  አገልግሎት እንዲሰጡም ቢሮው 25 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መድቦ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችን የማሟላት ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እንዲሁም የኮምፒዩተርና ሌሎች ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያግዙ ግብዓቶችን በቀጣይ ዓመት የማሟላት ስራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።

ትምህርት ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በሁለት ፈረቃ ከ80 ሺህ ያላነሱ ተማሪዎችን ተቀብለው እንደሚያስተናግዱም አስታውቀዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ የዶሮ ግብር አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ርዕሰ መምህር አቶ እሸቱ ጫኔ በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤቱ የተገነባው ተጨማሪ አንድ ብሎክ ህንፃ የነበረውን የክፍል ጥበት እንዳቃለላቸው ተናግረዋል።

አራት ክፍሎች ያሉት አንድ ብሎክ የመማሪያ ህንፃ ዘንድሮ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ተማሪዎች ሳይጨናነቁ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የክፍል ጥበት እንደነበረባቸው በማስታወስ  አሁን ግን በአዲስ በተገነባው ክፍል ሳይጨናነቁ ለመማር እንዳስቻላቸው የተናገረው  ደግሞ  የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ንጉሱ መርሴ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም