ኢትዮ ቴሌኮም የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን እየሰራ መሆኑን ገለፀ

181

ሀዋሳ/ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 17/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮ ቴሌኮም የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ለ32 ሚሊዮን ዜጎች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዘገባ ለማካሄድ ተግባራዊ እንቅሰቃሴ ውስጥ  መግባቱንም አስታወቋል።

ቴሌኮሙ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በደቡብ ሪጂን በሀዋሳ ከተማ ትላንት ባስጀመረበት ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ኢንፎርሜሽን ሲስተም ቺፍ ኦፊሰር አቶ እንዳለ አስራት እንደገለጹት ኢትዮ ቴሌኮም የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን እየሰራ ይገኛል።

ለዚህም መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎችን በመዘርጋት እንዲሁም አዳዲስ ዘመናዊ የዲጅታል መፍትሄዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን ሁሉን አቀፍ የቴሌኮምና የዲጅታል ፋይናንሻል አገልግሎት ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አውስተዋል።


 

በዚህ ረገድ የብሄራዊ ዲጅታል መታወቂያ የዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ  አስቻይ ሲስተሞች ውስጥ አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ኩባንያው በትላንትናው እለት በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ ዲጅታል መታወቂያ አዲስ አበባን ጨምሮ በ30 ከተሞች በይፋ መመዝገብ ማስጀመሩን ገልፀዋል።

በቀጣይም በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎቱ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ 90 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች መታወቂያውን ለማዳረስ መታቀዱን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ ቴሌኮም ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

"በዚህም የሀገራዊ እቅዱን 36 በመቶ የሚያከናወን ይሆናል" ያሉት አቶ እንዳለ ለዚህም ተፈጻሚነት በወር በዓማካይ 1 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመዝገብ መታቀዱን አስታውቀዋል።


 

የዲጅታል መታወቂያ ከዜጎች በሚወሰዱ መለያ አማካይነት የተረጋገጠ መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን ይህም ለቀልጣፋ ለአካታች የማህበራዊና ኢኮኖሚ እድገትና ለቢዝነስ ትስስር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ዜጎች ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደ ቀበሌ መታወቂያ፣የታደሰ መንጃ ፍቃድ፣ፓስፖርት፣ያሉ ሰነዶችን በመያዝ ወይንም የሰው ምስክር በማቅረብ በነፃ መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምእራብ ሪጅን ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ማስጀምሪያ መርኃ-ግብር ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የኢትዮ ቴሌኮም የዞንና የሪጅን ኮርዲኔሽን ዲፒውቲ ችፍ ኦፊሰር አቶ ሃይለሚካኤል ነቃ ጥበብ እንደገለጹት ኢትዮ ቴሌኮም የህብረተሰቡን የግንኙነት ስራ ከማሳለጥ ባሻገር ዘመናዊነት የሚያሳልጡ ስራዎች እያከናወነ ነው።

ከነዚህ ስራዎች መካከል ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ማዘጋጀት አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሰሜን ምእራብ ሪጅን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት አሰራሮች ተጠናቀው ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ደግሞ የሪጅኑ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ጥሩነህ ናቸው።

"ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ የእለት ተእለት ስራዎችን ቀላልና ቀልጣፋ በማድረግ የጎላ ሚና እየተወጣ ይገኛል" ብለዋል። 

በባህር ዳር ከተማ የተጀመረው የስራ እንቅስቃሴም በቅርቡ በደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ኮሶበር፣ ሞጣ፣ ቢቸናና ሌሎችም ከተሞች እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም